ከፍተኛ ሊግ | በወሳኝ ወቅት መሪነቱን የለቀቀው ነቀምቴ የፕሪምየር ሊግ ህልም

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም ነቀምቴ ከተማን እንመለከታለን።

[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]

ደረጃ፡ በ32 ነጥቦች 2ኛ (ከመሪው መድን በሁለት ነጥቦች ርቋል)

የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች

16ኛ ሳምንት፡ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ

17ኛ
ሳምንት፡ ከ ጉለሌ ክ/ከተማ

18ኛ
ሳምንት፡ ከ የካ ክ/ከተማ

ይህ የውድድር ዓመት የነቀምቴ ከተማን አጠቃላይ የክለብ ታሪክ ለመቀየር የተቃረበ ውድድር ዘመን ነው ማለት ይቻላል። ከፍተኛ ሊጉ በአዲስ መልክ በ2008 ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በውድድሩ ላይ የሚገኘው ክለቡ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ከነበረው ደካማ ተሳተፎ መሻሻል በማሳየት ከ2011 ጀምሮ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ችሏል። በ2011 3ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ፣ በ2012 ምድቡን ጥሩ አቋም ላይ ሆኖ እየመራ አንደኛውን ዙር ከፈፀመ በኋላ ውድድሩ በኮቪድ ምክምያት ተቋርጧል። ዓምና ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባለፈበት ምድብ ለ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ይህ በተከታታይ ዓመታት ወደ አናት የመጠጋት ልምድ መዳበር ቡድኑ ዘንድሮም በምድብ ሐ ሲደለደል ጥሩ ፉክክር ከሚያደርጉ ቡድኖች አንዱ እንደሚሆን የሚያስጠበቅ ነበር። እንደተጠበቀውም ነቀምቴ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ተስፋ ካላቸው ቡድኖች አንዱ መሆን ችሏል።

ከላይ እንደተጠቀሰው ቡድኑ በተከታታይ ዓመታት ካስመዘገበው ውጤት ባሻገር በከፍተኛ ሊግ ባልተለመደ መልኩ የተረጋጋ የቡድን ስብስብን ይዞ መቀጠሉ ለዘንድሮው ጉዞው ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገለት መናገር ይቻላል። ለአብነትም ዘንድሮ በዋና አሰልጣኝነት ነቀምቴን የተረከቡት የቀድሞው የቡድኑ አምበል እና ባለፉት ዓመታት በምክትል አሰልጣኝነት ከክለቡ ጋር የቆዩት አሰልጣኝ ተካልኝ ዳርጌ መሆናቸው እና ካስፈረማቸው ሰባት ተጫዋቾች ሦስቱ ከዚህ ቀደም በክለቡ የነበሩ መሆናቸውን ስንመለከት የላይኛውን ሀሳብ ያጠናክርልናል።

አሰልጣኝ ቾምቤ ገብረህይወትን በመተካት የውድድር ዓመቱን ከነቀምቴ ጋር የጀመሩት አሰልጣኝ ተካልኝ ዳርጌ ስለውድድር ዘመኑ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት

“ለዘንድሮው የ2014 ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ወደ ውድድርም ስንገባ ሂደቱ ጥሩ ነበር። በአንደኛው ዙር ጅማ ላይ አንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ ወደ ሀዋሳ ለሁለተኛው ዙር መጥተናል። ሀዋሳ ላይም እስከ አስራ አምስተኛው ሳምንት ድረስ ሳንሸነፍ ደርሰን ነበር። ውድድሩ በጣም የተሻለ ፣ የቡድናችን መንፈስም ጥሩ የነበረ ፣ ዳኝነነቱም ብዙም ወጣ ያለ ችግር ያላየንበት ነበር። ባለፈው ሳምንት በእግር ኳሱ ከሚያጋጥሙ ነገሮች አንዱ ከመድን ጋር ስንሸነፍ ገጥሞናል፡፡ እኛም ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች እየተዘጋጀን እንገኛለን። መድንም አልገባም ፤ ነቀምትም አልወጣም። በቀሩን ሦስቱ ጨዋታዎች ላይ አሸነፈን እንገባለን፡፡” ሲሉ የውድድር ዓመት ጉዟቸው እና ቀጣይ ህልማቸውን አስቀምጠዋል።
በእርግጥም አሰልጣኙ እንዳሉት ነቀምቴ ከተማ በመድን ሽንፈት እስኪገጥመው ድረስ ምድቡን ከጅምሩ እስከ 14ኛው ሳምንት ድረስ ሲመራ ቆይቷል። የውድድር ዓመቱን ደቡብ ፖሊስን 1-0 በማሸነፍ የጀመረው ነቀምቴ ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ከማሸነፉ በተጨማሪ በመሀል ከገጠሙት አምስት የአቻ ውጤቶች ውጪ ያለሽንፈት እስከመድኑ ጨዋታ መዝለቅ ችሎ ነበር። በተለይም የቡድኑ አስገራሚ የአንደኛ ዙር ግስጋሴ በመከላከል ጥንካሬ (ሦስት ግብ ብቻ ነው የተቆጠተበት) ታግዞ ከተፎካካሪው መድን በሦስት ነጥብ ርቆ እንዲያጠናቅቅ አድርጎት ነበር። በሁለተኛውም ዙር ነቀምቴ ጥንካሬው ባይከዳውም ያስመዘገባቸው ሁለት የአቻ ውጤቶች እና የመድኑ ሽንፈት ለተቀናቃኙ ቦታውን እንዲያስረክብ በር ከፍተዋል። አሰልጣኙም የዚህን ምክንያት ከአቋም መዋዠቅ ይልቅ ከጥቃቅን ስህተቶች ጋር ያያይዙታል።

“የውጤት መዋዠቅ ሳይሆን ነጥብ መጣል ነው፡፡ ነጥብ በእርግጥ ጥለናል ፤ መዋዥቅ የምንለው ግን ይህ ሂደት ለብዙ ሳምንታት ቢቀጥል ነበር፡፡ እስከ አስራ አምስተኛ ሳምንት ድረስ እየመራን ነበር፡፡ በእርግጥ አስራ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በመድን ጥለናል በጥንቃቅን ስህተቶች። መጀመሪያ በቅጣት ምት ጎል ተቆጠረብን ከዚያም በተጫዋች ስህተትም ሌላ ግብ አስተናገድን። ብዙ የመሳሳት ክፍተቶች ይታዩ ነበር፡፡ በቅያሪ እና በተለያዩ ነገሮች የሚቻለውን አድርገን ሳይሳካልን ቀርቷል ማለት ይቻላል፡፡”

ለረጅም ሳምንታት የዘለቀውን መሪነት ባሳለፍነው ሳምንት የተነጠቀው ነቀምቴ ዳግም ወደ ሰንጠረዡ ዓናት ተመልሶ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከፊቱ ሦስት ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቁታል። በእርግጥ ዕድሉ በመድን ነጥብ መጣል ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ከከፍተኛ ሊጉ ተገማች አለመሆን አንፃር ለነቀምት ፀሀይ ገና አልጠለቀችም። አሰልጣኝ ተካልኝም
“አዎ ቅድም እንዳነሳሁት ሦስት ጨዋታው ይቀራል። መድን አልገባም ነቀምት ከተማም አልወጣም ብዬ እንዳነሳሁት በሦስት ጨዋታ አይደለም በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ በሦስት ደቂቃዎች ብዙ ነገር ስለሚቀየር እስከ መጨረሻው ከየካ ጋር እስከምናደርገው ጨዋታ ድረስ በተስፋ ነው የምንጫወተው። ቡድናችን አሁንም ይገባል በሚለው ልጆች በተነሳሽነት በመመካከር ሲሰሩ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንደሚገባ እኛም እንደ ባለሙያ እየተጋን እንገኛለን ማለቴ ነው፡፡” በማለት ቀጣዮቹ ጨዋታዎች የማለፍ ዕድሉን ይዘውላቸው እንደሚመጡ ተስፋቸውን ይናገራሉ።

በቀሪዎቹ ወሳኝ ጨዋታዎች ከአቃቂ ቃሊቲ ፣ ጉለሌ እና የካ የሚጫወተው ነቀምቴ በተለይ ከየካ እና አቃቂ ጋር በሚኖሩት ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙ በመሆናቸው ቀላል ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም። ያም ሆኖ አሰልጣኙ ለጨዋታዎቹ ያላቸውን ዝግጅት ሲያስረዱ ጥረታቸው በመድን ነጥብ መጣል ካልያጀበ የሚመጣውን የመጨረሻ ውጤት በምን መልኩ እንደሚያስተናግዱት ካሁኑ የተዘጋጁበት ይመስላል።

“ለቀጣይ ጨዋታ እጅግ በጣም የተሻለ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው። አንድ ሁለት ልምምድ ላይ ተጫዋቾች ተሰምቷቸው ነበር። ከዛ መንፈስ ውስጥ እንዲወጡ አድርገን አሁን መደበኛ ልምምዳችንን በሚገባ እየሰራን ነው፡፡ መድን ውጤት ሊጥል ይችላል ብለን ስናስብ እኛም ነጥብ መጣል የለብንም ፤ እያሸነፍን ነው እነሱን የምንጠብቀው። ስለዚህ ሦስቱንም ጨዋታ በተሻለ ለማሸነፍ እንሰራለን ፤ የመጣውን ውጤት ደግሞ እንቀበላለን። ምክንያቱም እግርኳስ ውስጥ ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ። ያንን ደግሞ መቀበል ግዴታ ስለሆነ እኛ ሦስቱን ጨዋታ ማሸነፍ ነው የምናስበው። ቡድናችን ፕሪምየር ሊግ ይገባል ካልሆነ ደግሞ በፀጋ ተቀብለን ለሚቀጥለው በመስራት ችግራችን የቱ ጋር ነው የሚለውን እንደ አሰልጣኝ ቡድን በመነጋገር አስተካክለን ለመምጣት ለ2015 እንዘጋጃለን ማለት ነው፡፡”

ነቀምቴ ከተማዎች በ2011 ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩ መሆኑ እና በቀጣዩ ዓመትም ኮቪድ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ሊጉን እየመሩ ተስፋቸውን አለምልመው መቋረጡ ቁጭት እንዳሳደረባቸው የገለፁት አሰልጣኙ የአሁኑ ስብስባቸው ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመግባት አቅሙን ከእስካሁኑ መልካም ጉዞው ጋር በማገናኘት ይገልፁታል።

“ቡድኑ ትልቅ አቅም አለው። ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት አመላካች የሆኑ ነገሮችንም አይተናል። በእርግጥ እስከ አስራ አምስተኛው ሳምንት ድረስ ስንሄድ አቻ እየወጣን እያሸነፍን ነው የመጣነው። መድን ደግሞ ሲሸነፍም አቻ ሲወጣም ሲያሸነፍም የመጣ ስለሆነ ይሄ በቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ አይከሰትም ብሎ መጠበቅም ስህተት ነው። እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ነገሮች ከመጡ አሸናፊ ሆነን ቡድናችንን ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያስኬደው ጉዳና ውስጥ እንገባለን። ሦስቱን ካሸነፍን ሦስቱን ካሸነፉ በሁለት ነጥብ ከፕሪምየር ሊግ ውጪ እንሆናለን። ይሄንን ደግሞ በፀጋ ለመቀበልም ዝግጁ ነን ማለት ነው፡፡”

የተረጋጋው ቡድን የተነጠቀውን መሪነት መልሶ በማግኘት ህልሙን ያሳካል ወይንስ እንዳለፉት ዓመት ጫፍ ደርሶ ይመለሳል ?