[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም የምድብ ሀ መሪ ኤሌክትሪክን እንመለከታለን።
[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]
ደረጃ፡ በ32 ነጥቦች 1ኛ (ከተከታዮቹ በአራት ነጥቦች ርቋል)
የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች
16ኛ ሳምንት፡ ከ ሀላባ ከተማ
17ኛ ሳምንት፡ ከ ጌዴኦ ዲላ
18ኛ ሳምንት፡ ከ ባቱ ከተማ
የምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስም ከያዙ ክለቦች ዋነኛው ነው። በተለይም ከወጣት ቡድኑ በሚያሳድጋቸው ተጫዋቾች እና በጥሩ የምልመላ ሂደት በሚገነባው ጠንካራ ቡድን የጎላ ስም የነበረው “ኤልፓ” ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ለተከታታይ ዓመታት ላለመውረድ ሲጫወት ቆይቶ በመጨረሻም በ2010 የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ዋንጫ ካነሳበትና በአዲስ መልክ ሲጀመር ጀምሮ ተሳታፊ ከነበረበት ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ ተሰናብቷል። ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደ በኋላ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ተፎካካሪ መሆን ችሎ ነበር። በመጀመርያው ዓመት ሦስተኛ ፣ በቀጣዩ ዓመት ውድድሩ እስኪሰረዝ ድረስ ስምንተኛ፣ እንዲሁም ዐምና ወደ ሊጉ ያደገው መከላከያን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር።
ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ላለው እና የመፎካከር የሚያስችል መሠረት ያለው ታሪክ እና ስብስብ ባለቤት ለሆነው ቡድን ያለፉት ዓመታት ተፎካካሪነት በቂ ናቸው ማለት አይቻልም። ይልቁንም እንደ ሌሎች የአገልግሎት ተቋም ቡድኖች በወረደ ማግስት ‘ህልውናውን ያጣ ይሆን ?’ ከሚለው ስጋት በቀር በቶሎ ወደ ፕሪምየር ሊግ ይመለሳል የሚሉ ግምቶች ሚዛን ይደፉ ነበር። ያም ሆኖ ኤሌክትሪክ ከፍተኛ ሊግ በቀይ ምንጣፍ አልተቀበለው ኖሮ አዳማ እና መከላከያ ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ወደ ፕሪምየር ሊጉ በፍጥነት መመለስ ሳይሳካለት ቀርቷል።
ቀይ ለባሾቹ ዘንድሮ ግን ይሆን ታሪክ ለመቀየር የቆረጡ ይመስላሉ። ከአምና ጀምሮ የከፍተኛ ሊጉ ባለ ልምድ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን በመቅጠር ሁነኛ የሜዳ ላይ ለውጥ እያሳየ ይገኛል። ዓምና የመመለስ ምልክት አሳይተው ለጥቂት ወደ ኋላ የቀሩበትን ሊግ ዘንድሮ ለማሳካት ከየትኛውም ተሳታፊ በላቀ መልኩ ተቃርበዋል። የተጫወቱበትን ክለብ ከባለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ የተረከቡት አሰልጣኝ ክፍሌ ከዚህ ቀደም በሁለት ክለቦች እንዳደረጉት ሁሉ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማሳደግ ታሪካቸውን በኤሌክትሪክ ለመድገም እየተንደረደሩ ይገኛሉ። አሰልጣኙ በቀጣይ ለሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች እያደረጉ ስለሚገኙት ዝግጅት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የአራት ነጥብ ልዩነቱን አስጠብቆ ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቅ በእጃቸው ያለ መሆኑን አስምረውበታል።
“ዝግጅታችን ከሌላው ጊዜ የተለየ አይደለም፤ አንድ ዓይነት ነው። እንደተለመደው በየአራት ቀኑ ጨዋታ አለ። ለዛ የሚሆን ዝግጅት እንደለመድነው እያደረግን ነው። ክለብ ለክለብ እየለየን አንዘጋጅም። የአራት ነጥብ ልዩነት ብዙ አይደለም። ስለዚህ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ተከታዮቻችንም ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ ነው። ሁለተኛ እና ሦስተኛ የሚገኙት ባንክ እና ነገሌ አርሲ እርስ በእርስ ይገናኛሉ ፤ እኛ ግን የእነሱን መገናኘትም አንጠብቅም። እከሌ ነጥብ በጣለልን የምትልበት ነገር አይደለም። እጃችን ላይ ነው ያለው፤ ስለዚህ እንደ ሌላው ጊዜ ተጫውተን አሸንፈን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን። ለሦስት ጨዋታም ብለን ጭንቅላታችንን ወደ ሌላ ስሌት የምንከትበት ነገር የለም። በአጠቃላይ እንደ ሌላው ጊዜ ተዘጋጅተን እንጫወታለን። የምንመራበትን ነጥብ አስጠብቀን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን እንጂ እከሌ ይጥላል እከሌ ያሸንፋል የሚለው ውስጥ አንገባም።”
አስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሎ አምስት ተጫዋቾችን ከታች ቡድኑ ያሳደገው ኤሌክትሪክ ዝውውሮቹ ልምድ ባላቸው እና የከፍተኛ ሊግ አጨዋወትን ጠንቅቀው በሚያውቁት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጉ ለዘንድሮው ጉዞ የሰመረ መሆን አስተዋፅኦ ሳያደርግለት አልቀረም። በአዲስ መልክ ከተደራጀው ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ቡድን የስድስት ጨዋታ ድሎችን በሁለት አቻ ውጤቶች ብቻ አጅቦ ያለ ሽነፈት በጠንካራ ግስጋሴ የመጀመርያውን ዙር ማጠናቀቅ ችሏል። ሁለተኛውን ዙር በባንክ ተሸንፎ ቢጀምርም የሊጉ ክስተት ነጌሌ አርሲን ያሸነፈበት ጨዋታን ጨምሮ ወደ ድል በመመለስ ልዩነቱን አስፍቶ አሁን በፕሪምየር ሊጉ እና ኤሌክትሪክ መካከል ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተዋል።
በእርግጥ ኤሌክትሪክ ከተከታዮቹ ያለው ልዩነት የሰፋ መስሎ ቢታይም እስካለፈው ሳምንት ድረስ የገጠመው ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም። አሰልጣኝ ከፍሌም በተለይ በሁለተኛ ዙር ከባድ ፍልሚያ እንደገጠማቸው አልሸሸጉም። “በተለይ በሁለተኛ ዙር ጠንካራ ፉክክር ነው ያለው። ላለመውረድም ሆነ ለደረጃ ጠንካራ ፉክክር ነው የሚደረገው ፤ እከሌ የሚባል ክለብ የለም። ለምሳሌ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው አምቦ እኛን ነጥብ አስጥሏል። ከእኛ በፊት ደግሞ ጠንካራ የሚባለውን ጋሞ ጨንቻ አሸንፏል። ሻሸመኔ ከተማም በሁለተኛው ዙር በጣም ጠንክሮ ነው የመጣው። በመከራ ነው ከነሱ ላይ ውጤት ያገኘነው። እያንዳንዱ ጨዋታ ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል። በአንደኛው ዙር እንደ አሁኑ ብዙ ፈተና አልነበረንም። እኛም የአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ስለነበረን ያንን ለማስጠበቅ እና ላለመጣል በጥንቃቄ ስንጫወት የሥነ ልቦና ጫና መጥቶብን ነበር። እዚህ የምንጫወትባቸው ሜዳዎች ለሁሉም ምቹ ናቸው። መጫወቻ ሜዳው ብቻ ሳይሆን መለማመጃ ሜዳዎቹም አመቺ ናቸው። በአጠቃላይ በሁለተኛው ዙር ውድድር ክለቦቹ ጠንክረው ነው ያገኘሁዋቸው። በጣም መሻሻል ያሳዩ ክለቦች አሉ ፤ ሁሉም ማለትም ይቻላል። እያንዳንዱ ጨዋታ ፈተና ነበረው። በደረጃ ወረድ ያለ ቡድንም ሜዳ ላይ ጠንካራ ብቃት ነው የሚያሳየው። የምንጫወተው ደግሞ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ስለሆነ ከተለያየ ክልል የመጡ ተማሪዎች አሉ። እነሱ ተማሪዎች ደግሞ የመጡበት ከተማን ከፍተኛ ድጋፍ ነው የሚሰጡት። ደመቅ ያለ ውድድር ነው። ትልቅ ፉክክር እየተደረገ ነው። በቀጣይም ቀላል ጨዋታዎች አይሆኑም። እኛም ጨዋታዎቹን በትኩረት ለመቅረብ እንሞክራለን። ከሦስቱ ሁለቱን ብናሸንፍ የማለፍ ዕድል ስላለን የምንችለውን እናደርጋለን። ግን እከሌ ጠንካራ ነው እከሌ ደካማ ነው ማለት ፈፅሞ አይቻልም።” ሲሉ የምድቡን ጥንካሬ እና የገጠማቸውን ፉክክር ያስረዳሉ።
በቀጣይ ኤሌክትሪክ ሦስት ጨዋታዎች ከፊቱ ይጠብቁታል። በተለይ ዛሬ 4፡00 ቀጥተኛ ተፎካካሪዎቹ ነጌሌ አርሲ እና ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ፤ የቡድኖቹ አቻ መለያየት ወይም መሸናነፍ በኤሌክትሪክ ጉዞ ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅእኖ ከመሆኑ አንፃር ኤሌክትሪክ በትኩረት የሚከታተለው ጨዋታ እንደሚሆን እሙን ነው። ሆኖም አሰልጣኝ ክፍሌ ያን ያህል ትኩረት እንዳላደረጉበት በጠቆሙበት አስተያየታቸው “ሁለቱ እርስ በእርስ መገናኘታቸውን ብዙም ትኩረት አላደረግንበትም። እኛ የሚያዋጣን ከፊት ለፊታችን ያለውን ጨዋታ ማሸነፍ ነው። ነገሌ አርሲ ክስተት ነው። መጀመሪያ ሆሳዕና ላይ እያሸነፉ ሲመጡ ብዙም ትኩረት አላደረግንባቸውም ነበር። በኋላ ላይ ጨዋታቸውን ስናይ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን መያዛቸውን አወቅን። ከፊት እስከ ኋላ ጥሩ ተጫዋቾች አሏቸው። እኔ እዚህ ደረጃ ይደርሳሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር። አመጣጣቸው የሚያስፈራ ነበር። ባህር ዳር ከመጣን በኋላም እነሱም ይጥላሉ ፤ እኛም እንጥል ነበር። ንግድ ባንክ ደግሞ እየተሻሻለ የመጣ ቡድን ነው። ቡድኑ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ደግሞ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው። ክለብ ያሳደጉ ተጫዋቾችም አሉ። ሰበታ እና ፋሲልን ያሳደጉ ተጫዋቾችም ስላሉ ውድድሩን ያውቁታል። ስለዚህ እንደ አዲስ ቡድን አይደሉም። ሁለቱም ቢገናኙም ካላሸነፍን ዋጋ የለውም። እኛ ትኩረታችን የራሳችን ጨዋታ ላይ ነው። ቢሆንም ግን አቻም ቢወጡ እንዲሁም አንዱ ቢያሸንፍ አንዱ ይቀራል። ከዛ ሁለት ጨዋታ ብቻ ስለሚቀር ፉክክሩ የሦስት የሚለው ይቀርና የሁለት ይሆናል። ስለዚህ ለእነሱም ወሳኝ ነው። እኛም እንዳልኩት እከሌ ቢጥል አንልም። ትኩረታችን ከፊታችን ያለው ጨዋታ ላይ ነው። በአጠቃላይ የእኛም ሆነ የእነሱ ጨዋታ ከባድ ነው።” ብለዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁን ላይ ለምድቡ የበላይነት መቃረብ ቢችልም በአንደኛው ዙር ከነበረበት ጥንካሬ አንፃር በሁለተኛው ዙር የአቋም መዋዠቅ አጋጥሞት ታይቷል። ከስድስት ጨዋታ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት ማስመዝገቡም ይህን የሚያሳይ ነው። ሆኖም የነጌሌ አርሲ መንሸራተት እና ንግድ ባንክ በአንደኛው ዙር የጣላቸው በርካታ ነጥቦች ኤሌክትሪክ ስጋት ውስጥ እንዳይገባ አድርጎታል። ቡድኑ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መዋዥቅ ውስጥ የገባበትን እና ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ውስጥ እንዲገባ ያስገደደውን የሁለተኛ ዙር ሂደት አሰልጣኝ ክፍሌ እንዲህ ገልፀውታል።
“መጀመሪያ ወደ ባህር ዳር ስንመጣ ብዙ መበላለጥ አልነበረም። ባንክ ዕድልን ይዞም ቢሆን የመጀመሪያውን ጨዋታ አሸነፈን። ያ ሽንፈት ለቡድናችን የመጀመሪያ ሽንፈት ነበር። ያ በአዕምሮ አወረደን። እግር ኳስ ደግሞ ዋናው አዕምሮ ነው። ያ ጨዋታ ያላሰብኩት ጨዋታ ነው። አቻም ብንወጣ ቢከተለንም ይሻል ነበር። እግር ኳስ ላይ ያሸንፍ የተባለ ቡድን ያሸንፋል። ባላሰብነው ነገር ተሸነፍን። ከተሸናፊነት ወደ አሸናፊነት መምጣት ከባድ ነው ፤ ከዛ ግን አሸነፍን። አንድ ዙር ሙሉ መርተን እነሱ መሪነቱን ሊቀበሉን ሁሉ ነበር። ግን እነሱም ነጥብ ይጥሉ ነበር። የባንክ ብቻ ሳይሆን የነገሌም ነጥብ መጣል ሞራል ሰጠን። እነሱም ይጥላሉ እኛም እንጥላለን። ከዚህ መነሻነት መሪነታችን እንደተጠበቀ ሆነ። ነገርግን ያልተሸነፈ ቡድን ሲሸነፍ በስነ ልቦና የሚያጋጥመው ነገር ይታወቃል። ያንን መሸነፍ እያሰቡ መጫወት ጫና ነበረው። የትኛውም ቡድን ደግሞ ሰማይ ነክቶ አይሄድም። መሸነፉ አይቀርም። አንዳንዴ መውረድ አለ። ተጫዋችም ሳታስበው ይወርዳል። መልሰህ ክፍተቶችን አርመህ ወደ ትክክለኛ ቦታ መምጣት ነው። ነገርግን የነጥቡ ልዩነት የአንድ ነጥብ ስለሆነ ስጋቱ አለ። በሁለተኛ ዙር ዝግጅት በርቀት እንመራለን ብለን ነበር ተነጋግረን ስንሰራ የነበረው። ባላሰብነው ምልኩ ነጥቡ እየጠበበ ሄደ። ነጥብ ከጣልን ደግሞ ከስር ያለው አሸናፊ ቡድን መሪነቱን ይረከባል። ይሄ በተወሰነ መልኩ በአዕምሮ ረገድ የተወሰነ እንዳንረጋጋ አድርጎናል። ከዚህ ጫና ውጪ ምንም ድክመት የለም ነበር። እንደውም ጥሩ ተጫዋቾችን ጨምረን ነው ሁለተኛውን ዙር የጀመርነው። ነገርግን ያ የመጀመሪያው ሽንፈት አስተዋፅኦ አድርጎ በአዕምሮ የመውረድ ነገር ተከስቶ ነበር። የሚገርመው ተከታዮቻችንም ነጥብ ይጥሉ ነበር። አሁን ያ የነጥብ ልዩነት ከአንድ ወደ አራት መጥቷል። ስታሸንፍ ሁሌ በራስ መተማመን ይመጣል። ያ የጭንቀት ጊዜም ሄዶ ጥሩ ላይ ነው ያለነው።”
ቡድኑ በሁለተኛ ዙር ለገባበት ጫና ወደ ፕሪምየር ሊግ ካለፉ ከክለቡ ቃል የተገባላቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ያለው አስተዋፅኦም እዚህ ጋር ሳይጠቀስ አይታለፍም። በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት አሰልጣኝ ክፍሌ ” ከፍተኛ ሊግ ላይ ይታወቃል የፊርማ ገንዘብ የለም፤ ደመወዝ ነው ያለው። እኔን ጨምሮ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ደግሞ የደሀ ልጆች ናቸው። በሚገኝ ገንዘብ ህይወት የማይቀየር ከሆነ በኋላ ያስቸግራል። ይሄንንም ተጫዋቾች ያስባሉ። ቃል የተገባልን ገንዘብ የሚያነሳሳ ቢሆንም በጠቀስኩት ምክንያት በአዕምሮ ደረጃ ጫና ውስጥ መክተቱ አይቀርም። አንድ ጊዜ እንደውም የሆነ ጨዋታ ካሸነፋችሁ ተብሎ ቃል ተገብቶ አላሸነፍንም። እና ይሄ ነገር ጭንቀት ይፈጥራል ማለት ነው። ይሄንን ገንዘብ አግኝቼ የሆነ ነገር ባደረኩ ስትል ጫናው ይመጣል። ኳስ ስትጫወት ደግሞ ነፃ ሆነህ ነው መሆን ያለበት። በጣም ጎበዝ ተጫዋች ብትሆንም አዕምሮህ ነፃ ሆኖ ካልተጫወተ የምታስበውን ነገር ሜዳ ውስጥ ማድረግ አትችልም። በዚህኛው ሳምንት ግን ፈጣሪ ይመስገን ነገሮች መስመር እየያዙልን ነው። ተጫዋቾቹ ልምምድ ላይም ያስታውቃሉ በራስ መተማመናቸው እንደመጣ።”ሲሉ ገልፀዋል።
ከጫናውም ሆነ ከአቋም መወዠቅ ባሻገር ኤሌክትሪክ ከየትኛውም ቡድን በተሻለ ስለ ፕሪምየር ሊጉ ማሰብ የጀመረ ክለብ ነው። ከዚህ ቀደም አየር ኃይል ፣ ጅማ አባ ጅፋር (አንደኛ ዙር) እና ሰበታ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ የሚታወቁት አሰልጣኝ ክፍሌም ለሌላ ታሪክ መቃረባቸው ደስተኛ ያደረጋቸው ይመስላል። የሜዳ ላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ብቻ ሳይሆን መገፋትን ድል ስለመንሳታቸው የሚጠቁም ሀሳብ አካፍለውናል። “ፈጣሪ ይመስገን። እዚ ሀገር ትገፋለህ። ነገርግን ዋናው ነገር ተገፍተህ እንደገና ከታች ተነስተህ ወደ ላይ መምጣት ነው። እኔ ሰበታ ተገፍቻለው። ይሄ ግልፅ ነው። አንድ ሳይሸነፍ ያደገን ክለብ ይዜ በፕሪምየር ሊጉ መስራት ነበረብኝ። ግን ልምድ የለውም ተብሎ እኔ ቁጭ ብዬ ሦስት አሠልጣኝ ቀያየሩ። ያኔ ሞራሌ ስለተነካም አልሰራም ብዬ ስድስት ሰባት ወር ተቀምጬ ነበር። የምትለፋው ለሽልማት ብቻ አይደለም። ላይም ሄደህ የሰራከውን ስራ ለማሳየት ነው። ተስፋ ቆርጬ ነበር። ዓምናም ኤሌክትሪክ ምድቡ ላይ ተፎካካሪ ነበር። ሀዋሳ ላይም የፕሪምየር ሊግ ቡድኖችን ሲያሸንፍ ታይቷል። በአብዛኛው ወጣቶችን ነበር የያዝኩት። ይሄኛው ዓመት ላይ ደግሞ ከዓምናው ስህተቶች ተምረን የቀረብንበት ነው። ተገፍተህ እና አዕምሮው ሞቶ ከታች ለፍተህ እዚህ ደረጃ መድረሱ ትልቅ ነገር ነው። ፈጣሪዬንም አመሰግናለው። በጎ ዐምሮ ካለህ ትነሳለህ። እኔ ተገፍቼ በዛው አልቀረውም። ተነስቼ እዚህ ደረጃ ደርሻለው። ይሄ ትልቅ ነገር ነው። ማንም ሰው ተስፋ መቁረጥ የለበትም። በርትቶ ከተሰራም ምንም መሆን ይቻላል።”
በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም ያለው ኤሌክትሪክ ከሦስት ዓመታት ሙከራ በኋላ ከፕሪምየር ሊጉ መግቢያ ደጃፍ ደርሷል። “እናልፋለን። ሁለት ጨዋታ እየቀረን ወደ ሊጉ እንደምናድግም አስባለው።” ሲሉም አሰልጣኝ ክፍሌ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። በእርግጥ ኤሌክትሪክ ከሁሉ ቀድሞ የ2015 ፕሪምየር ሊግን ትኬት ይቆርጥ ይሆን ?