[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም የምድብ ሐ መሪ ኢትዮጵያ መድንን እንመለከታለን።
[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]
ደረጃ፡ በ34 ነጥቦች 1ኛ (ከተከታዩ በሁለት ነጥቦች ርቋል)
የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች
16ኛ ሳምንት፡ ከ ጉለሌ ክ/ከተማ
17ኛ ሳምንት፡ ከ የካ ክ/ከተማ
18ኛ ሳምንት፡ ከ ደቡብ ፖሊስ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተመልካች ተወዳጅ ከሆኑ ቡድኖች እንዱ የነበረውና የብዙዎች ”ሁለተኛ ቡድን” የነበረው ኢትዮጵያ መድን ከ1990ዎቹ መጨረሻ ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያለው ተፅዕኖ እየተዳከመ ከፕሪምየር ሊግ መውረድ እና መውጣት መለያው ሆኖ ቆይቷል። ይባስ ብሎ ደግሞ በ2006 ሊጉን ከተሰናበተ በኋላ በተለያዩ ዓመታት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ሲያደርግ የነበረው ትግል ሳይሳካ ቀርቷል።
ወጣቱ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድን በድጋሚ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ በመቅጠር ወደ ውድድር የገባው ኢትዮጵያ መድን ዓምና 3ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ስብስብ ላይ በከፊል ለውጥ በማድረግ 11 ተጫዋቾች ከማስፈረሙ ባሻገር 6 ወጣቶች አሳድጎ አሰልጣኙ አዘውትረው በሚሰሯቸው ቡድኖች ውስጥ እንደሚያስመለክቱት እና ዕምነታቸው መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተው በሚገልፁበት መልኩ በአንፃራዊነት ወጣት የሚባል ስብስብ በመያዝ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎን የማሳካት ህልም ይዞ ነበር የጀመረው። ሆኖም ወላይታ ሶዶ ከተማን አሸንፎ በድል የጀመረው ዓመት በተከታታይ በጅማ አባ ቡና ሽንፈት አስተናግዶ ከሀምበሪቾ አቻ መለያየቱ ድንቅ አጀማመር ካደረገው ነቀምቴ ከተማ ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጎት ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ቅኝት መግባት በመቻሉ ግን አራት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና ሁለት ጨዋታ አቻ በመለያየት ከነቀምቴ ያለውን ልዩነት ወደ ሦሰት ዝቅ በማድረግ አንደኛውን ዙር አጠናቋል።
” ውድድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ትልቁ ነገር ጠንካራ እና እያንዳንዱን ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ከመሆኑ አኳያ ፣ ቡድኖች ሁሉ ለማሸነፍ እና ቻምፒዮን ለመሆን ካላቸው ፍላጎት አንፃር ፣ እንደገና ደግሞ ተጫዋቾችም ሜዳ ላይ የሚያሳዩት ተጋድሎ ሲታይ ውድድሩ ጠንካራ እና ጥሩ ፉክክር እየታየበት ያለ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ስለ ውድድር ዓመቱ ሀሳባቸውን መስጠት የጀመሩት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ እንደየጨዋታዎቹ ባህርይ በሚያደርጉት ተለዋዋጭነት ውጤታማ ስለመሆናቸው እምነታቸውን ገልፀዋል። ” በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉንም ቡድን በዕኩል ደረጃ ነው የምናየው። ሁለተኛ ደግሞ እንደ ጨዋታው የራሳችንን ጨዋታ ይዘን ነው የምንገባው። እንደገና ጨዋታውንም አይተን እዛው የታክቲክ ለውጦችንም በማድረግ ለምሳሌ ጨዋታውን ብልጫ በመውሰድ በመከላከልም በለው በማጥቃትም በአንድ ለአንድም በለው ወይም ኳስን በመቆጣጠር ረገድም በለው በየትኛውም የኳስ ሂደቶች ሜዳ ላይ የሚገጥሙንን ነገሮች ብልጫ ለመውሰድ እና ለማሸነፍ ነው የምንገባው። ሌላው ደግሞ የታክቲካል ፍሌክሴብሊቲ ብዙ ጊዜ ተገማች እንዳንሆን ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ነው የሚጫወቱት ብለው ሲሉ እኛ ደግሞ በተጋጣሚያችን ደካማ ጎን ላይ ተመስርተን በአንድ ጨዋታ ላይ በአንድ ጊዜ ሦስት የጨዋታ ለውጦችን ልናደርግ እንችላለን። በይበልጥ እኛ አድቫንቴጅ የምናገኝበትን ከለራችንን ሳንለቅ ግን የእኛን ዕድል በሚያስጠብቅ መልኩ እንደዚህ ዓይነት ሂደቶችን መጠቀማችን ነው። ምን አልባት ከዛ አንፃር ይመስለኛል ተገማች የማይሆነው፡፡” በማለት የቡድኑን አጠቃላይ ጉዞ እና የውጤታማነታቸውን ምስጢር ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ መድን በአንደኛው ዙር ያሳየውን መሻሻል በሁለተኛው ዙር ይበልጥ አሳድጎ በእጅጉ የጠነከረ ቡድን ይዞ ቀርቧል። ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ከ18 ነጥብ 16 ማሳካቱን መመልከት በራሱ የቡድኑን መሻሻል የሚመሰክር ነው። ከዚያም ባለፈ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር 1 ጎል ብቻ ማስተናገዱ እና መሪ የነበረው ነቀምቴን ማሸነፉ ጥንካሬውን የሚገልፅ ነው። በሁለተኛው ዙር መሻሻሎች መታየታቸውን ቢጠቁሙም ቡድናቸው ከጅምሩ ወጥ የሆነ አቋም ስለማሳየቱ እንዲህ ይገልፁታል። “አንደኛው ምን አልባት አንደኛውን ዙር ብታዩትም ምንም ከዚህ ያነሰ ብቃት አልነበረም። በአንደኛ ዙር የሜዳዎች አለመመቻቸት ፣ የልምምድ ሜዳ ምቹ አለመሆን ጅማ ላይ በነበርንበት ወቅት እነኚህ እና ሌሎች ችግሮች ነበሩ፡፡ ከዚህ ጋር ካልሆነ ወጥ የሆነ አቋም ነው ያለን ብዬ ነው የማምነው። አንደኛው ዙርም ጥሩ ጨዋታ ነበር። በጣም ተጭነን ነው ስንጫወት የነበረው በጣም የጎል ሙከራዎችንም እናደርጋለን። አንደኛው ዙር የነበረው ሁኔታ ይሄ ነው። ሁለተኛ ዙርም ላይ ምን አልባት አንደኛ ዙር ላይ ካስመዘገብነው የተሻለ ውጤት መመዝገቡ የአንደኛ ዙር ወጥነት ነው ብዬ ነው የማምነው እንጂ ከአንደኛው ዙር የጣልናቸው ነጥቦች በስህተቶች ነው፡፡ በስህተቶች ምክንያት ነው ውጤት ያጣነው እንጂ ወጥ ነበርን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ”
በእርግጥም ቡድኑ በቁጥራዊ መመዘኛዎች መሻሻሉ ቢታይም በአንደኛው ዙር የነቀምቴ ጥንካሬ የመድንን ውጤታማነት መሸፈኑ ዕሙን ነው። በሁለተኛው ዙር ያሳየው አስደናቂ ጉዞም በነቀምቴ መጠነኛ መዋዠቅ መደገፉ እንዲሁ። በተለይም ባለፈው ሳምንት ለረጅም ጊዜ ምድቡን ሲመራ የቆየው ቀጥተኛ ተፎካካሪው ነቀምቴን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2-0 ማሸነፉ በወሳኝ ወቅት መሪነቱን እንዲጨብጡ አድርጓቸዋል። “ድሉ በጣም ተነሳሽነትን ይፈጥራል ፤ እውነት ለመናገር የነቀምቴ ቡድን ረጅም ጊዜ ሲመራ ነበር፡፡ የቅርብ ተፎካካሪያችን ነው ፤ እግር በእግር እየተከታተልነው ስለሆነ መጨረሻ ላይ እርስ በእርሳችን ተገናኘን። አሁን የቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ናቸው እና አሸንፈነው መሪነቱን መቀበላችን በጣም ትልቅ ደስታን ፈጥሮልናል። እምደገና ለቀጣዮቹም በደንብ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ተነሳሽነቱ እንዳለ ሆኖ ከአሁን በኋላም ያሉት ካለፍነው የበለጠ በጣም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንዳለን ነው የሚሰማኝ። በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው ፤ የቀሩን ቡድኖች በጣም ጠንካራዎች ናቸው፡፡የሚቀረውን እንግዲህ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው ማለት ነው፡፡” ሲሉ ይህ ድል ከፍተኛ ተነሳሽት የሚፈጥርላቸው ስለመሆኑ እምነታቸውን ገልፀዋል።
ከጉለሌ ክ/ከተማ ፣ የካ ክ/ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሚቀሩት መድን የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ዕድል አግኝቶ ጨዋታዎቹን ያደርጋል። ስለ ቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኙ “እየተዘጋጀን ያለነው በሥነ ልቦና ነው፡፡ ያው ሌላ ጊዜ የምናደርገውን ዝግጅት ነው እያደረግን ያለነው። በተለይ ግን በሥነ ልቦናው መዘናጋቶች እንዳይኖሩ የበለጠ ተጠንቅቀን ቀጣዮቹንም ጨዋታዎች እናደርጋለን። በማሸነፍ ላይ ተመስርተን በሌሎች ጊዜያቶች እንደምንዘጋጀው ግን የበለጠ ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ ” በማለት ዝግጁነታቸውን ሲገልፁ “እስከ አሁን ታግለን ዕድሉን በእጃችን አስገብተናል። ከአሁን በኋላ ባሉት ጨዋታዎች ሌሎች ቡድኖች ላይ ጥገኛ ሆነን አንጫወትም። በቃ የኛን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የምንወስንበትን አጋጣሚ አግኝተናል። እና ይሄንን ቢያንስ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ከፈጣሪ ጋር ቀጣዮቹንም ጨዋታ እናሸንፋለን ብዬ ነው የማስበው፡፡” ሲሉ አክለዋል።
ከዚህ ቀደም የአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ረዳት በመሆን አዲስ አበባ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ የረዱት አሰልጣኝ በፀሎት በ2011 መድንን እየመሩ ከወልቂጤ ከተማ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው እስከመጨረሻው ዘልቀው ከፕሪምየር ሊጉ ደጃፍ ተመልሰው ነበር። ዘንድሮ በድጋሚ ወደ መድን የተመሱት አሰልጣኙ በድጋሚ ቡድኑን ከጫፍ ያደረሱት ሲሆን በዚህ ዓመት እንደሚሳካላቸው ተስፋ አድርገዋል። “ደስ የሚል ስሜት ነው ያለው። የዛን ጊዜም እንገባለን ብለን ነበር፤ ብዙ ባላሰብናቸው ምክንያቶች ነው የተበላሸብን። የአንድ ነጥብ ልዩነት ነበር የነበረን እና የዛን ጊዜም በጣም ቆጭቶኝ ነበር። የተሻልን ቡድን ነበርን ፣ ፍፁም የበላይነት ነበረን። የዛን ዓመት የነበረው ቡድን በጣም ጠንካራ ቡድን ስለነበር እንገባለን ብዬ አስቤ ነበር ፤ አልተሳካም። አሁን ደግሞ እድላችን እጃችን ላይ ነው ያለው። ፈጣሪ መጨረሻችንን ያሳምረው። ያኔ ያልተሳካውን ደግሞ አሁን ስታሳካው ደስ ይላል። እንግዲህ መጨረሻው ይመር ነው የምንለው፡፡”
የውድድር ዘመኑን እንደ ረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር የሩጫውን መሪ እግር በእግር በመከታተል ጉልበት ሲሰበስብ ቆይቶ ደውሉ ሲደወል አፈትልኮ የሚወጣ አትሌትን አምሳያ የያዘ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ኢትዮጵያ መድን አሁን ላይ ደውሉ ሲደወል ማፈትለክ ጀምሯል።
መድን ሩጫውን ምድቡን በበላይነት ጨርሶ ወደ ፕሪምየር ሊግ በመግባት ያጠናቅቅይሆን ?