የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ልምምድ ጀመሩ

ከአስራ አራት ቀናት በላይ ከክፍያ አለመፈፀም ጋር በተያያዘ ልምምድ አቁመው የሰነበቱት የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ወደ ዝግጅት ገብተዋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በበርካታ ጉዳዮች ጥያቄ እየተነሳበት የሚገኘው ሰበታ ከተማ ለፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች የካቲት 29 ለተጫዋቾቹ ጥሪ በማድረግ ወደ ዝግጅት ለመግባት ቢያስብም ተጫዋቾቹ አለም ገና በሚገኘው መገርሳ ባቱ ሆቴል ከተሰባሰቡ በኋላ የተጠናቀቀው የ2013 የውድድር ዘመን እና የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከሰባት እስከ ሦስት ወራት ያህል የደመወዝ ክፍያ ካልተፈፀመ አንጀምርም በማለታቸው ለአስራ አራት ያህል ቀናት ልምምድ ሳይሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን ጉዳይ ተከትሎ የክለቡ ተጫዋቾች የመልቀቂያ ደብዳቤ አልፎም ደግሞ ያረፉበትን ሆቴል ለቀው ወጥተው የነበረ ሲሆን በትላንትናው ዕለት የክለቡ አመራሮች ከክለቡ ተጫዋቾች ጋር ባደረጉት ውይይት የክለቡ አመራሮች ያለፈውንም ሆነ የዘንድሮውን አመት ክፍያ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን ተጫዋቾችም የተባለው ክፍያ በተቀመጠው ቀን ካልተፈፀመ በድጋሚ እንደሚያቆሙ በመግለፅ ሁለቱ አካላት በዚህ ከተስማሙ በኋላ በዛሬው ዕለት ማለዳ 12፡30 ላይ በሰበታ ስታዲየም በአሰልጣኝ ብርሃን ደበሌ መሪነት ወደ ልምምድ ቡድኑ መመለሱን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ያጋሩ