የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 16ኛ ሳምንት የዛሬ የጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሻገረው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምር ስልጤ ወራቤ እና ሰንዳፋ በኬ ድል ሲቀናቸው ኮልፌ እና ካፋ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በቀዝቃዛማው ዐየር ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ስልጤ ወራቤን ከቂርቆስ አገናኝቶ ስልጤ ወራቤ ከመመራት ተነስቶ 2-1 አሸንፏል።

ገና በጨዋታው ጅማሮ ወደግብ በመድረሱ ረገድ ተሽለው የቀረቡት ቂርቆሶች በጊዜ መሪ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ ስልጤ ወራቤዎች ጨዋታውን ቀለል ያለ ግምት የሰጡ በሚመስል መልኩ መዘናጋት ይታይባቸው ነበር። በ7ኛው ደቂቃም አጀማመራቸውን ያሳመሩት ቂርቆሶች ቀዳሚ ሆነዋል። ጎሉንም በጥሩ ቅብብሎሽ ወደ ፊት በመሄድ ናትናኤል ታረቀኝ አስቆጥሯል።

ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ትኩረት አድርገው መጫወት የጀመሩት ወራቤዎች በ13ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ተሻግሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው እና ሳዲቅ ሴቾ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ ቡድኑን ወደ ጨዋታ ለመመለስ የነበረውን ጥረት ማሳያ ነበሩ። ቂርቆሶች በመጀመርያው አስር ደቂቃ የነበራቸው መልካም እንቅስቃሴ እየወረደ መጥቶ ዕረፍት እስከወጡበት ጊዜ ድረስ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ አልቻሉም ነበር። በተቃራኒው ወራቤዎቸ ግልፅ የጎል ዕድል አይፍጠሩ እንጂ ደጋግመው ወደ ጎል የመድረሳቸው ጥረት አጠናክረው በመቀጠል የአቻነት ጎል አግኝተዋል። ጎሉንም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳዲቅ ሴቾ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን በ39ኛው ደቂቃ አቻ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ በስልጤ ወራቤ የበላይነት ቀጥሎ የመጀመርያው ጎል በተቆጠረበት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በ55ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመምታት ለራሱም ሆነ ቡድኑን መሪ ያደረገች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ ሳዲቅ ሦስተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችልበትን አጋጣሚ አግኝቶ ወደ ኳሱን ወደ ጎል ቢመታውም የቂርቆሱ ግብ ጠባቂው ዳግም አራጌ አምክኖበታል። ቂርቆሶች ኳሱን ለመቆጣጠር ቢያስቡም የጠራ የጎል አጋጣሚ እምብዛም አልፈጠሩም። በአንድ አጋጣሚ ተቀይሮ የገባው የግራ መስመር ተከላካዩ አቤል ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመታው እና ግብ ጠባቂው እንደምንም ያዳነበት አጋጣሚ ብቸኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። በአንፃሩ ወራቤዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት የተሻሉ አጋጣሚዎች ቢያገኙም ካለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በቀላሉ ኳሶች እየተበላሹ ይባክኑ ነበር። ጨዋታውም በዚህ ሂደት ቀጥሎ ተጨማሪ ጎል ሳያስመለክተን በስልጤ ወራቤ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ቂርቆሶች ሁለት ጨዋታ እየቀረ ከወዲሁ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።

ስምንት ሰዓት ሰንዳፋ በኬ እና ካምባታ ሺንሺቾ ያገናኘው ጨዋታ በሰንዳፋ በኬ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ጎል መቆጠር የጀመረው ገና የዳኛው ፊሽካ እንደተሰማ ነበር። ሰንዳፋ በኬዎች ያስጀመሩትን ኳስ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ፎሳ ሳንዲቦ በፍጥነት በማምለጥ በ1ኛው ደቂቃ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዮት ካምባታዎች ጥሩ የጎል ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በሁለቱም በኩል በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ጨዋታው ሳቢ ሆኖ በቀጣለበት አጋጣሚ ሰንዳፋዎች ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ጎሉንም በ6ኛው ደቂቃ አቤል ታምራት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል። ይህ ጎል የተቆጠረበት ሂደት የካምባታው የህክምና ባለሙያ ህክምና ሰጥቶ ከሜዳው ሳይወጣ ዳኛው በማስጀመሩ የተቆጠረ ጎል ነው በማለት የጎሉን መፅደቅ ካምባታዎች ተቃውመው ነበር።

ብልጫ ወስደው ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ሰንዳፋ በኬዎች አቤል በጥሩ ሁኔታ ተጫዋች አልፎ ከአጨራረስ ችግር ያልተጠቀመበት ኳስ የሰንዳፋን የጎል መጠን ከፍ በየምታደርግ ነበረች። በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ካምባታዎች በተደጋጋሚ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ይድረሱ እንጂ የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ነበር። የኋላ ኋላ በ69ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ክብሮም ፃደቁ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎት ግብ አግኝተዋል። በዚህ የማጥቃት ሂደት የቀጠሉት ካምባታዎች ለማመን የሚከብድ ለጎሉ አንድ ሜትር ርቀት ላይ አጥቂው ድልነሳው ሺታው አግኝቶ ያልተጠቀመበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ሰንዳፋዎች ውጤት ለማስጠበቅ በጥንቃቄ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ጫና ሲፈጥሩ ካምባታዎች በበኩላቸው ጠንካራውን የሰንዳፋን በኬን የመከላከልን አጥርን አልፈው ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በሰንዳፋ በኬዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር የተመከትንበት የአስር ሰዓት ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮን ከካፋ ቡና አገናኝቶ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኮልፌዎች ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ስንታየሁ ሰለሞን በረጅሙ የተሻገረለትን በግብጠባቂው አናት ላይ ከፍ አድርጎ በማሳለፍ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ኮልፌዎች በጥሩ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥረው ብልጫ ወስደው ይጫወቱ እንጂ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጋላጭ ነበሩ። በዚህም እንቅስቃሴ ወደ ፊት የሄዱት ካፋ ቡናዎች በ24ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቷ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ታከለ ታንቱ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ መታተር ያሳዩት ካፋ ቡናዎች በ56ኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ታከለ ታንቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋች ቀይረው ቢያስገቡም በጨዋታ መሀል በሚሰሩ አላስፈላጊ ጥፋቶች ጨዋታው እየተቆራረጠ ወደ አሰልቺነት አምርቷል። ጨዋታው በካፋ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ሲባል ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ተስፈኛው ወጣት አብርሃም አሰፋ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ከሽንፈት የታደገች ጎል አስቆጥሯል። የጨዋታው መገባደጂያ ላይ የካፋ ቡናው አጥቂ ሱራፌል ፍቃዱ ምላሱ በመንራተት የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋቱ ምክንያት በስፍራው የነበረውን የስፖርት ቤተሰብን ያስደነገጠ ሲሆን ለተሻለ ህክምና ወደ ሆሲፒታል አምረቶ አሁን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠናል። ጨዋታውም በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ያጋሩ