የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የ16ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የዛሬ ፍልሚያዎች ወሳኙ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ባቱ ከተማም እንዲሁ በተመሳሳይ ድል አስመዝግቦ የሻሸመኔ እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተቋጭቷል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ባቱ ከተማ ገላን ከተማን 1-0 ረትቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ እና አደገኛ የሆኑ ሙከራዎች አልተስተዋሉም። ሆኖም ግን በጊዜ ጨዋታውን መምራት ችለው የነበሩት ባቱዎች ውጤታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። ባቱ ከተማዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ክንዳለም ፍቃድ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ነበር ጨዋታውን በእጃቸው ማስገባት የቻሉት።

በሁለተኛው አጋማሽ አስጨንቀው የተጫወቱት ባቱ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ባይችሉም በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። 56ኛ ደቂቃ ላይ ሃኒካ ሄይ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ጥሩ የሚባል ሙከራ ሆኖ ታይቷል። በድጋሚ 60ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ ሳጥን ጠርዝ የተገኘውን የቅጣት ምት ዳዊት ቹቹ ወደ ግብ በቀጥታ ሞክሮ የግብ ቆሚ የመለሰበት በሁለተኛው አጋማሽ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ባቱ ከተማዎች በዚህ መልኩ ብልጫ ወስደው በተደጋጋሚ በመስመር የሚሻሙ ኳሶችን ሲጠቀሙ ለገላን ከተማ ተከላካዮች አስቸጋሪ ነበሩ። 63ኛው ደቂቃ ላይ የሽጥላ ዳቢ በግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ጌታሰጠኝ ሸዋ በጥሩ ሁኔታ ቢቆጣጠረውም ኳሱን ግን መጠቀም አለቻለም። ከደቂቃዎች በኋላ ጌታሰጥኝ ሸዋ በሦስት ተጫዋቾች መሀል ቆንጆ ኳስ አሸልኮ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢያገናኘውም ያሬድ ወንድማገኝ ወደ ሁለተኛ ግብነት መቀየር አልቻለም። ባቱዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ያገኙትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል። በአንፃሩ ገላን ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽም የረባ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።


ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በሚደረገው ፍልሚያ ውስጥ ወሳኝ ድል አሳክቷል። 8:00 በተደረገው ከመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመቀጠል የተቀመጡትን ነገሌ አርሲ እና ንግድ ባንክን ባገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሻለ ኳሱን አደረጃቶ የመጫወት ብልጫን ወስዷል። ንግድ ባንኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው 13 ደቂቃ ብቻ ነበር። ከመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ በመጠቀም አደም አባስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ግሩም ግብ አስቆጥሯል። በድጋሚ 27ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር አደም አባስ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻምቶት የዋላሸት ሰለሞን በጭንቅላት ቢገጭም አላማውን አልጠበቀም። በነገሌዎች በኩል ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ወደ ባንክ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በአብዛኞቹ አጋጣሚዎች ኳስ ከተከላካዮች አልፋ ለአጥቂዎቻቸው መድረስ አልቻለችም። ሆኖም ግን የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ወንድማገኝ ሊሬ አስቆጥሮ ነገሌዎችን አቻ ማድረግ ችሏል ።

ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ነገሌዎች ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም ጨዋታውን ለመቆጣጠር በቅተው ነበር። ያም ቢሆን ንግድ ባንኮች በመስመር የሚያደርጓቸው ፈጣን እንቅስቃሴዎች እጅግ አስፈሪ ነበረ። በባንክ በኩል 60ኛው ደቂቃ ላይ አደም አባስ በቀኝ መስመር ግብ ጠባቂውን አልፎ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ተጠግቶ የወጣበት ቅፅበት የሚያስቆጭ ነበር። በድጋሚ 66ኛው ደቂቃ ላይ አብዱሰላም የሱፍ ከርቀት የመታው ኳስ በሙከራ ደረጃ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።

ከመሀል የሚሰነጡ ኳሶችን በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የዋላሸት ሰለሞን እና አደም አባስ በተደጋጋሚ ተከላካዮችን ጥለው በመውጣት የነገሌዎችን ተከላካይ ክፍል ሲያስጨንቁ አስተውለናል። በዚሁ አኳኋን 70ኛው ደቂቃ ላይ የኋለሸት ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ድንቅ ግብ በማስቆጠር በድጋሚ ባንክን መሪ ማድረግ ችሏል ። በነገሌዎች በኩል 75ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ቶማስ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂ የመለሰበት የሚጠቀስ አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል።


ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አንድ ሲያጠብ በቅርብ ተፎካካሪዎቹ ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው የነገሌ አሪሲ ጉዞ ግን ተስተጓጉሏል።

በዕለቱ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ እና ሻሸመኔ ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል።

10:00 ሰዓት ላይ በነበረው ሻሸመኔ ከተማ ከ ጋሞ ጨንቻ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራ ደረጃ ሻሸመኔዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ፀጋየ ባልቻ ከግብ ጠበቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ከቀረው አጋጣሚ ውጪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚጠቀስ ጠንካራ ሙከራ አልነበረም።

ከዕረፍት መልስም ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ ጨዋታ ዘይቤ ያልተጠቀሙት ሁለቱ ቡድኖች በሙከራ ደረጃ ጋሞዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ አስጨናቂ ፀጋዬ በጭንቅላት ገጭቶት ኢላማውን ያልጠበቀው እንዲሁም በሻሸመኔ በኩል 86ኛው ላይ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው አጋጣሚ ብቻ ተጠቃሽ ሲሆኑ ጨዋታውም ያለግብ የተጠናቀቀ ሆኗል።