የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 16ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ16ኛው ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ በሁለተኛው ዙር መሻሻሎችን ያሳየው ሀምበሪቾ ዱራሜ ድል ሲቀናው ሶዶ ከተማም ጅማ አባ ቡናን 1ለ0 አሸንፏል፡፡ ነቀምቴ ከተማ በአንፃሩ ከ አቃቂ ቃሊቲ ጋር ያለ ጎል አጠናቆ ወደ መሪነት የሚመልሰውን ዕድል አምክኗል፡፡

ሀምበርቾ ዱራሜ በመልካም አቋሙ ቀጥሏል

የምድብ ሐ የአስራ ስድስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ የሆነው ጨዋታ በሀምበሪቾ ዱራሜ እና ደቡብ ፖሊስ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ የሦስተኝነት ቦታን ለመቆናጠጥ የሰፋ ዕድል ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨውታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የመሰለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ቢያስመለክተንም በሚገባ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ እና ጥቃት በመሰንዘሩ ረገድ የአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞው ሀምበሪቾ ዱራሜ እጅጉን የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ማሳያ ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ምንያምር ጴጥሮስ ከቀኝ የፖሊሶች የግብ ክልል ወደ መስመር ካደላ ቦታ የተገኘን ቅጣት ምት ሲያሸማ ልዑልሰገድ አስፋው በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በወጣበት ሙከራ ቀዳሚዎቹ ሆነዋል፡፡በመስመር በአላዛር አድማሱ በመሀል ሜዳ ላይ በዮሴፍ ድንገቶ ፣ ስንታየው አሸብር እና አቤል ዘውዱ አስደናቂ ጥምረት ታግዘው በልዩነት ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል፡፡

8ኛ ደቂቃ ላይ የመስመር ተከላካዩ ምንያምር ጴጥሮስ በግራ የደቡብ ፖሊስ የማዕዘን መምቻ ዳር የተገኘን ቅጣት ምት ሲያሻማ አምበሉ እንዳለ ዮሐንስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር በተራራ ስያሜ የሚጠራውን ክለብ ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ወደ ግብ ለመድረስ ሲቸገሩ በሚስተዋሉት ቢጫ ለባሾቹ በከል ከመስመር ተሻምቶ ኤልያስ እንድሪስ ገጭቶ የሳታት እና 11ኛ ደቂቃ ላይ ዳንኤል መቆጮ ከግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡15ኛው ደቂቃ ላይ ሰይፈ ዛኪር ላይ የደቡብ ፖሊሱ ተከላካይ ሞገስ ቱሜቻ ከግቡ ትይዩ ቦታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት የቀድሞው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ተጫዋች ምንያምር ጴጥሮስ አክርሮ ሲመታ የግብ ጠባቂው ደሳለኝ ንጉሴ የአያያዝ ድክመት ታክሎበት ሁለተኛ ግብ ሆና ተቆጥራለች፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ልክ አራት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ በቀኝ የደቡብ ፖሊስ ሳጥን በኩል ዮሴፍ ድንገቶ እና ምንያምር ጴጥሮስ ከመሠረቱት ኳስ መነሻነት ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂ ታሪኩ አረዳ ስህተት ታክሎበት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ አጥቂ ሰይፈ ዛኪር ሦስተኛዋን ጎል ከመረብ አዋህዶ ወደ 3-0 አሸጋግሯል፡፡ ሦስት ግቦችን ለማስተናገድ ከተገደዱ በኋላ ወደ ደቡብ ፖሊሶች ወደ ጨዋታ ቅኝት ቢገቡም ጥቅጥቅ ብሎ ወደ መከላከል የተሸጋገሩት ሀምበሪቾዎች በቀላሉ አላስከፍት ሲሉ ተስተውሏል፡፡

ይሁን እንጂ ኤርሚያስ ደጀኔ ያሻማትን ኳስ ዮናስ ወልዴ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ወደ 3-1 የአሰልጣኝ አላዛር መለሰን ቡድን ማድረግ ችሏል፡፡ ሀምበሪቾዎች በአላዛር አድማሱ ደቡብ ፖሊስ በብሩክ ዳንኤል የማግባት ዕድልን ቢያገኙም ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው 3-1 ተደምድሟል፡፡

ሶዶ ከተማ ጅማ አባ ቡናን በጠባብ ውጤት አሸንፏል

የቀኑ ሁለተኛ መርሀግብር 8፡00 ሰዓት ሲል በሶዶ ከተማ እና ጅማ አባቡና መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን የሚከተሉት ሁለቱ ቡድኖች ረጃጅም የሆኑ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ማጥቃት ወረዳው በመጣል ግቦችን ለማግኘት የጣሩበት ሂደት ቡድኖቹ ለማጥቃት የመረጡት የአጨዋወት መንገድ እንደነበር በደንብ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያው አጋማሽ አልፎ አልፎ ኳስን በመቆጣጠር ለመጫወት ፍንጭ ያሳዩ የነበሩት ሶዶ ከተማዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል የተሻገረን ኳስ አላዛር ፋሲካ ሲጨርፈው የወላይታ ድቻ ፍሬ የሆነው ፊኒያንስ ተመስገን በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ላይ ግሩም ጎል በማስቆጠር ሶዶን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡

ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ካገኙት አቅጣጫ ሁሉ ወደ ጎል በመሞከር ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያልተለያቸው ጅማ አባ ቡናዎች በቀድሞው የወላይታ ድቻ ተጫዋች መልካሙ ፉንዱሬ አማካኘት ባደረገው ሙከራ ወደ ግብ ደርሰዋል፡፡በተለይ 23ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ቃሲም ከቅጣት ምት ያገኘውን ኳስ ሲመታ ግብ ጠባቂው አቡሽ አበበ አውጥቶበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዞ በጀመረው የሁለቱ ጨዋታ ይህ ነው የሚባሉ ዕድሎች ለመመልከት ብዙም አልታደልንም። ነገር ግን የሶዶ ከተማ የመከላከል እና የጅማ አባ ቡና አደገኛ አጨዋወት በይበልጥ ጎልቶ መታየት የቻለበትን አጋማሽ አስተውለናል፡፡ የሶዶ ከተማው ጥበቡ ከበደ ግልፅ የማግባት አጋጣሚን አግኝቶ 74ተኛ ደቂቃ ላይ ካመከናት ብቸኛ የጠራች ሙከራ ውጪ ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በሶዶ ከተማ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ነቀምቴ ከተማ መሪ መሆን የሚችልበትን ዕድል አምክኗል

ጠንካራ ፉክክር ነገር ግን ኃይል የተቀላቀለበት እና ፀብ አጫሪ ድርጊቶችን ባስተዋልንበት የነቀምቴ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ 10፡00 ሰዓት ሲል ጀምሯል፡፡ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በአመዛኙ ማየት በቻልንበት ቀዳሚው አጋማሽ አቃቂ ቃሊቲዎች አቀራረባቸውን ከቀደመው አጨዋወታቸው አሻሽለው ኳስን መሠረት ባደረገ የጨዋታ መንገድ ለመጫወት ሲታትሩ ሲስተዋል ወደ ምድቡ መሪነት ለመሸጋገር የሚረዳውን ጨዋታ ያደርግ የነበረው ነቀምቴ ከተማ በሚታወቅበት ተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

ጨዋታው በተጀመረ አምስተኛ ደቂቃ ላይ አምበሉ ቴዎድሮስ መንገሻ ባመከናት ግልፅ አጋጣሚ ነቀምቴዎች በሙከራ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ ኳስን በአንድ ሁለት ለመጫወት ጥረት ባልተለያቸው አቃቂ ቃሊዎች በኩል እስማኤል አደም ከቅጣት በቀጥታ መትቶ በግብ ጠባቂው ሌሊሳ ታዬ አማካኝነት ከሽፎበታል፡፡ መደበኛው የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊገባደድ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ጉልላት ተሾመ የግል አቅሙን ተጠቅሞ በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት ተመልሶበታል፡፡

ጭቅጭቅ ፣ ንትርክ እና አሰልቺ የሆኑ የሜዳ ላይ እንቅሴቃሴዎች በተበራከቱበት ሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ ተጫዋቾች ከዳኛ ጋር የሚገቡት እሰጥ አገባ የጨዋታውን ቅርፅ ሙሉ በሙሉ አደብዝዞታል፡፡የአሰልጣኝ ተካልኝ ዳርጌው ነቀምቴ ከተማ የተሻለ የማጥቃት ኃይልን በተጠቀመበት በዚህኛው አጋማሽ 51ኛው ደቂቃ ላይ ከነቀምቴ ተከላካይ በረጅሙ የተላከ ኳስ ተቀይሮ የገባው ዳንኤል ዳዊት ለማግኘት ሲሮጥ ኳሱን ለማስጣል ግብ ጠባቂው ቢኒያም ሀብታሙ እና ተከላካዩ ከድር አድማሱ ሲረባረቡ ኳሷ ሾልካ የግቡ መስመር ላይ ስትደርስ ተጫዋቾች ተረባርበው ያወጧት ሲሆን በዚህ ሂደትም የአቃቂው ተከላካይ ከድር አድማሱ ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ደርሶ ተጫዋቹ እስኪታከም ጨዋታው ለአምስት ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ቀጥሏል፡፡


አቃቂ ቃሊቲዎች በአሸናፊ ካሳ ነቀምቴ ከተማ በዳንኤል ዳዊት አማካኝነት የግብ አጋጣሚን ቢያገኙም ከመረብ አንድም ጎል ማረፍ ሳይችል ጨዋታው 0ለ0 ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የነቀምቴ ከተማ የቡድን አባላት በዕለቱ ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ እና በአወዳዳሪ አካል ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ነገሩም እየከረረ ሄዶ የፀጥታ ኃይል እና ተጫዋቾች እርስ በእርስ ወደ ፀብ ገብተው ለ30 ደቂቃ ያህል የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ነገሮች ረግበው ሁሉም ወደየመጣበት አምርቷል፡፡