ከፍተኛ ሊግ | ቡራዩ ከተማ ከፍተኛ ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጎ ያስደንቀን ይሆን ?

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም የምድብ ለ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡራዩ ከተማን እንመለከታለን።

[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]

ደረጃ፡ በ28 ነጥቦች 2ኛ (ከመሪው ለገጣፎ ለገዳዲ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሏል)

የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች

16ኛ ሳምንት፡ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

17ኛ ሳምንት
፡ ከ ቡታጅራ ከተማ

18ኛ ሳምንት
፡ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ

ቡራዩ ከተማ የ2014 የውድድር ዓመትን የጀመረው ዓምና ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የተፎካከረ ቡድኑን አጠናክሮ ወይም ባለፈው ዓመት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው የነበረበትን ድክመት አርሞ አልነበረም። በቀጥታ ከአንደኛ ሊግ አድጎ እንጂ።

የከፍተኛ ሊግ የውድድር ባህርይ ፈታኝ ከመሆኑ አንፃር ቡራዩ ከተማ ዘንድሮ በተቀላቀለው ሊግ ላይ ወጥ አቋም አሳይቶ ለረጅም ሳምንታት የምድቡ መሪ ሆኖ መዝለቁን መመልከት አስገራሚ ነው። ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ የነበረውን መሪነት ቢነጠቅም ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት አንድ ብቻ መሆኑ እና ዛሬም ተጋጣሚው መሪው ለገጣፎ መሆኑን ከግምት ስናስገባ ቡራዩ ከተማ አሁንም የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎን በማሳካት ከአንደኛ ሊግ ባደገበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ ታሪክ መስራት የሚችልበት እድሉ በእጁ ላይ አለ።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በአዲስ መልክ በ2008 ሲጀመር ተሳታፊ ከነበሩ ክለቦች አንዱ የነበረው ቡራዩ ተፎካካሪ መሆን ባይችልም ለቀጣዮቹ አራት የውድድር ዘመናት የሊጉ ላይ ተሳታፊ ከመሆን አላገደውም ነበር። ሆኖም በ2011 ባስመዘገበው ደካማ ውጤት ሊጉን ተሰናብቷል። ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት በአንደኛ ሊጉ የተዳከመ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ሊጉ በመቋረጡ በሊጉ ለመቀጠል እና ያለፈ ድክመቱን ለማረም ዕድል ማግኘት ችሏል። በ2013ም ራሱን አሻሽሎ ከምድቡ ወደ ማጠቃለያ ውድድር የሚያልፈበትን ውጤት አስመዝግቦ በአዳማ በተከናወነው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ በአሰልጣኝ መኮንን ማሞ እየተመራ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል። በግማሽ ፍፃሜ እንዲሁም በፍፃሜው ጨዋታ ላይ ቡራዩ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ አቻ ቢለያይም በወንድወሰን ገረመው ድንቅ ብቃት ታግዞ በውጤታማ የመለያ ምቶች የውድድሩ ቻምፒዮን መሆን ችሏል።

ቡራዩ ከተማ ይህን የውድድር ዓመት የጀመረው ከ 11 በላይ ተጫዋቾች አስፈርሞ የዋናው አሰልጣኝ መኮንን ማሞ እና ረዳቱ ጳውሎስ ፀጋዬን ጨምሮ የቡድኑ ግማሽ ስብስብን ውል በማራዘም ነበር። ቡድኑ እንዲያድግ ወሳኝ ሚና የተጫወተው ወንድወሰን አሸናፊን ቢያጣም በፕሪምየር ሊጉ እና ከፍተኛ ሊጉ የመጫወት ልምድ ያላቸው ጥቂት ተጫዋቾችን በማከል ነበር ወደ ውድድር የገባው። ያም ሆኖ ዝውውሮቹ ይህን ያህል ርቀት የሚያስጉዘው ነው ብሎ የገመተ አልነበረም።

ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ቡራዩ በቀጣይ ያደረጋቸውን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድቡን መምራት ቻለ። በተከታታይ ሁለት አቻ ውጤቶች ቢመጡም በሁለት ድል አንደኛውን ዙር 21 ነጥቦች ላይ ደርሶ በቀዳሚነት ያጠናቀቀው ቡራዩ ከተፎካካሪዎቹ ወጥ ያልሆነ አቋም ጋር ተዳምሮ በአንደኛው ዙር ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውለታል።

በአሁኑ ሰዓት ከምክትል ወደ ዋና አሰልጣኝነት በመሸጋገር ቡድኑን እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ ቡራዩ ከተማ ወደ ሊጉ በተቀላቀለበት ዓመት ውጤታማ የሆነበትን ምስጢር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሲያስረዱ ” እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት እኛ አንደኛ ሊግ ነበርን። ወደ ከፍተኛው ሊግ ማደግ አለብን ብለንም ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ ዝግጅት ስናደርግ ነበር። ፈጣሪ አሳክቶልን ዋንጫ አንስተን ወደ ከፍተኛ ሊግ አድገናል። ከፍተኛ ሊግ ከገባን በኋላም ብዙ ተጫዋቾችን አልጨመርንም። ይልቁንም እስካሁን ላመጣነው ውጤት ትልቁ ሚስጥር የተጫዋቾች ህብረት ፣ አንድነት ፣ መተሳሰብ እና እርስ በእርስ ያለን ግንኙነት ነው። ከዚህ በተጨማሪም የተጫዋቾቹ ፍላጎት ተደምሮ እስካሁን ያለውን ውጤት ይዘን መጥተናል።” በማለት ከዝውውሮች ይልቅ የቡድን ህብረት ለዚህ እንዳበቃቸው ጠቁመዋል።

በአንደኛው ዙር ከነበረው ጥንካሬ በተጨማሪ በተከታዮቹ ወጥ አለመሆን ምክንያት ሁነኛ ፉክክር ያልገጠመው ቡራዩ የሁለተኛው ዙር ግን ፈታኝ ሆኖበታል። ለገጣፎ ለገዳዲ ራሱን አሻሽሎ ሲቀርብ ቤንች ማጂ ቡና ደግሞ ባልተገመተ መልኩ ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ ይበልጥ ተጠግቶታል። ቡራዩም ቢሆን በሁለተኛ ዙር ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ብቻ አሸንፎ ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥብ 7 ብቻ ማሳካቱ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርጎት በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት መሪነቱን ለለገጣፎ አሳልፎ ለመስጠት ተገዷል።

በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው ዙር የነበራቸውን ጥንካሬ የመቀነሳቸው ምክንያት የልምድ አለመኖር፣ ጉዳት እና በተጫዋቾች ላይ የተፈጠረው ጉጉት እንደሆነ አሰልጣኝ ጳውሎስ ያምናሉ። ” እንደታየው ብዙዎቹ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው ፤ የበሰሉ ተጫዋቾች ብዙ የሉንም። እንደተባለውም በሁለተኛው ዙር እንደ አንደኛው ዙር ውጤት አላመጣንም። የተጫዋቾችም ጉዳት አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለይ የተከላካይ ፣ የአጥቂ እና አማካይ መስመር የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ተጎድተውብን ነበር። ይህ የተጫዋቾች ጉዳት በደንብ ጎድቶናል። ሌላው ተጫዋቾቹ ላይ የታየው ጉጉት ነው። የነጥቡ መቀራረብም ተጫዋቾቹ ላይ ጭንቀቶችን ፈጥሯል። ይሄ ጭንቀት ውጤቶችን አበላሽቶብን ነበር። በዋናነት ግን ጠንካራ ጎናችን የነበሩትን ነገሮች ጉዳት አበላሽቶብናል ፤ በተለይ የተከላካይ መስመራችን ላይ። ወሳኝ ሦስት ተከላካዮቻችን እና የምንተማመንበት አጥቂ ገና አሁን ነው አገግመው መጫወት የጀመሩት። ”

ቡራዩ አሁን ወደ ሁለተኛ ዝቅ ቢልም መልሶ መሪነቱን የሚቆናጠጥበት ዕድል ከፊቱ ይጠብቀዋል። ከምድቡ መሪ ለገጣፎ ጋር ዛሬ 10:00 ላይ የሚያደርገው ጨዋታን በአግባቡ ከተጠቀመ ለረጅም ጊዜያት ወደነበረበት መሪነት መመለስ ይችላል። ከተሸነፈ ደግሞ ልዩነቱ ወደ አራት የሚሰፋ በመሆኑ ታሪክ የመስራት አጋጣሚው በእጅጉ ጠባብ ይሆናል። ከዚህ አንፃር ወሳኝ ለሆነውም ሆነ ለመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ ግብሮች ዝግጅት እንዳደረጉ አሰልጣኝ ጳውሎስ ነግረውናል። ” በባለፈው ጨዋታ የታዩ ድክመቶች አሉ። እነዛን ድክመቶች አርመን ለለገጣፎው ጨዋታ እየተዘጋጀን ነው። ያለው ዕድል ለሁለታችንም ዕኩል ነው። ሆኖም እኛ ማሸነፍ ነው ያለን አማራጭ። ይሄንን ጨዋታም ለማሸነፍ ባለችን ቀሪ ጊዜ ድክመታችንን አርመን ውጤት ይዘን እንወጣለን ብለን እንጠብቃለን። በቀሪዎቹም ጨዋታዎች ጥሩ ነገር ለማምጣት ተጫዋቾቹን በሥነ-ልቦናው ረገድ እያዘጋጀን ነው። ለተጫዋች ሥነ-ልቦና ወሳኝ ነው። ከዚህም መነሻነት ትልቅ ሥራ እየሰራን ነው። ቀሪ ጨዋታዎች ጠንካራ ናቸው። በተለይ የማክሰኞው ጨዋታ ወሳኝ በመሆኑ ለዚህ ጨዋታ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ነው። ፈጣሪ ይጨመርበትና ቀሪዎቹን ጨዋታዎች እናሸንፋለን ብለን ነው የምናስበው።” ብለዋል።

በእርግጥ የከፍተኛ ሊግ የውድድር ፎርማት ጥቂት ጨዋታዎች የሚደረጉበት እና በአንድ ቦታ የሚከናወን በመሆኑ ፉክክሩ ለሁሉም ቡድኖች ክፍት ቢሆንም በወሳኝ የመጨረሻ ወቅቶች ላይ ያሉ ጫናዎችን ተቋቁሞ ውጤታማ መሆን የሚችሉት ጥቂቶች ናቸው። ጥሩ ግስጋሴ አድርጎ በወሳኝ ሰዓት መንሸራተት የጀመረው ቡራዩስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ አቅሙ አለው ወይ የብዙዎች ጥያቄ ነው። አሰልጣኝ ጳውሎስም ለዚህ ጥያቄ ያላቸው ምላሽ በተስፋ የተሞላ ነው። ” ከተፎካካሪዎች አንፃር ለገጣፎ ጥሩ ቡድን ነው። እኛ ጋርም ከጉዳት ያገገሙ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች አሉ። እኛ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንገባለን ብለን ነው የምናስበው። እንዳልኩት ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾች መመለሳቸው ለእኛ ተስፋ ነው። ስለዚህ ሙሉ ሆነን ስለምንገባ ጨዋታዎቹን አሸንፈን ወደ ፕሪምየር ሊግ ብዬ አስባለሁ።”

ቡራዩ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ ባደገበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ አዲስ ታሪክ ለማፃፍ ከፊቱ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ይቀሩታል። ከባዱን ፉክክር በድል ተወጥቶ ያስደንቀን ይሆን ?