[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም የምድብ ለ መሪ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲን እንመለከታለን።
[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]
ደረጃ ፡ በ29 ነጥቦች 1ኛ (ከተከታዩ ቡራዩ ከተማ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ ተቀምጧል)
የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች
16ኛ ሳምንት፡ ከ ቡራዩ ከተማ
17ኛ ሳምንት፡ ከ ቂርቆስ ክ/ከ
18ኛ ሳምንት፡ ከ ሰንዳፋ በኬ
ለገጣፎ ለገዳዲ በከፍተኛ ሊጉ ያለው የተሳትፎ ታሪክ እና ተፎካካሪነት መሳ ለመሳ ናቸው። በ2009 ሊጉን የተቀላቀለው ለገጣፎ በአንፃራዊነት ዐምና ሸርተት ከማለት ውጪ በተሳተፈባቸው የከፍተኛ ሊግ ውድድሮች ሁሉ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሏል። በተለይም በ2011 ከምድቡ የበላይ ሆኖ ካጠናቀቀው ሰበታ ከተማ ጋር እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ ትግል አድርጎ ሳይሳካለት ሲቀር በ2012 ደግሞ ምድቡን እየመራ ኮቪድ 19 ተከስቶ የፕሪምየር ሊግ ህልሙ ተሰናክሏል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለገጣፎ ዐምና ከኩድኑ ጋር ከነበሩት ዋና አሰልጣኙ ጥላሁን ታደሰ ጋር ቀጥሏል። ቡድኑን ለማዋቀር በሄደበት መንገድም የቀደመ ወሳኝ ተጫዋቹ ልደቱ ለማን ጨምሮ 17 አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የዋና ዋና ተጫዋቾችን ውል በማደስ ራሱን አጠናክሮ ለፍልሚያው ቀርቧል።
ለገጣፎ የውድድር ዓመቱን የጀመረው አሁን እንዳለበት ደረጃ አስደሳች በሆነ ሁኔታ አልነበረም። የውድድሩ መክፈቻ በነበረው ጨዋታ በሺንሺቾ 3-0 ተሸንፎ ሊጉን የጀመረው ለገጣፎ በቀጣዩ ሳምንት ስልጤ ወራቤን በማሸነፍ ቢያገግምም በድጋሚ በኮልፌ ቀራኒዮ ሽንፈት ገጥሞት ጥሩ ያልሆነ አጀማመር አድርጎ ነበር። ሆኖም ቀስ ቀስ ባሳየው ማንሰራራት ከእንቅልፉ በጊዜ በመንቃት በቀጣይ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስቱን በማሸፍ ነጥቡን 19 አድርሶ ከመሪው ቡራዩ የነበረውን ልዩነት በሁለት ነጥቦች አጥብቦ የመጀመርያውን ዙር መጠናቀቅ ችሏል።
የቡድኑ አቋም ተስተካከሎ ወደ ዕረፍት ማምራቱ ይበልጥ ቡድኑን ያጠናክረዋል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ሆኖም የአንደኛ ዙር የአጀማመር ችግሩ በሁለተኛው ዙርም በድጋሚ አገርሽቶበታል። በተከታታይ ሦስት መርሐ ግብሮች ጨዋታውን ያለ ግብ አቻ የተለያየው ለገጣፎ የምድቡ መሪ የነበረው ቡራዩም በተመሳሳይ ጥሩ ያልሆነ ጉዞ አደረገ እንጂ እንደ አጀማመሩ ቢሆን አሁን ያለበትን ቀዳሚ ስፍራ ማግኘት ተራራ መውጣት በሆነበት ነበር። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ የታየበት የወጥነት ችግር ውጤት ለማግኘት ከመጓጓት የተፈጠረ እንደሆነ አብራርተዋል። ” የሰበሰብናቸው ተጫዋቾች ጥሩ ችሎታ ያላቸው እና በዲስፕሊንም የታነፁ ናቸው። ወጣት ከመሆናቸው የተነሳ ግን ትልቅ ጉጉት አለ። ከዛ አንፃር ነው እንጂ ከችሎታ አንፃር አይደለም። ለማሸነፍ ካለ ፍላጎት ነው መዋዠቁ የሚታየው እንጂ በሁለተኛው ዙር ያልተሸነፉ ቡድኖች እኛ እና ቤንች ማጂ ነን። ማሸነፍ ኖሮብን ሙሉ ነጥብ ያላገኘንባቸው ጨዋታዎች ነበሩ። ምክንያቱ ደግሞ ከጉጉት እና ከመጣደፍ የመጣ ነው። እሱን በቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች አሰተካክለን ማሸነፍን እያሰብን እንሰራለን። ”
ከሦስቱ ተከታታይ የሁለተኛ ዙር የመክፈቻ ጨዋታ አቻዎች በኋላ የድል መንገዱን መልሶ ያገኘው ለገጣፎ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፎ ከጠንካራው ቤንች ማጂ ጋር ደግሞ አቻ በመለያየት መሪነቱን በ29 ነጥቦች መቆናጠጥ ችሏል። በተለይም በመጨረሻ ያከናወነው የቤንች ማጂውን ጨዋታ በበላይነት ቢወጣ ኖሮ የፕሪምየር ሊግ መንገዱን ያደላድል ነበር። አሰልጣኙ ቡድኑ አሁን ላይ እየታየበት ያለው መነቃቃት ከሜዳ ላይ በተጨማሪ የአስተዳደር ስራዎችም አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቆም አድርገዋል። ” ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ መሪነት የመጣነው ፤ በአንድ ነጥብም ቢሆን የምድቡ መሪ ነን። ያለን ስብስብ የተሻለ ነው። ጥሩ መስራት እንደሚችሉም ተጫዋቾችን በአዕምሮ ረገድ የማነሳሳት ሥራ እየሰራን ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባውም ሜዳ ድረስ እየመጡ ውድድሮችን ያያሉ። የሚያስፈልጉ ድጎማዎችንም ያደርጋሉ። ተጫዋቾችን የማነሳሳት ሥራ ይሰራሉ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የከተማው ወጣቶች እና ስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ እዚህ እየመጡ ውድድሩን እያዩ የቡድኑን ተነሳሽነት ከፍ እያደረጉልን ነው። ከዛ አንፃር ነው መነሳሳቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው።” በማለት ወደ መሪነት የመጡበት ሂደትን አብራርተዋል።
የለገጣፎ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ዕጣ ፈንታን የሚወስኑ ሦስት ጨዋታዎች ከፊቱ ቢገኙም ይበልጥ ዛሬ 10:00 ላይ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ አንገቱ ስር እየተነፈሰ ከሚገኘው ቡራዩ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በእጅጉ ወሳኝ ነው። ለሁለቱ ቡድኖች ማሸነፍ እጅግ አስፈላጊ እንደመሆኑም በከፍተኛ ትኩረት እና ዝግጅት የሚደረግ ጨዋታ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ፍልሚያው ቀላል እንደማይሆን የገለፁት አሰልጣኙም ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። ” ከቡራዩ ጋር የሚኖረን ጨዋታ ከባድ ነው። ተቀራራቢ ውጤት ነው ያለን ከዛም አልፎ ደግሞ የደርቢ ስሜት ያለው ጨዋታ ነው። በጨዋታው የራሳችንን ጠንካራ ጎን በመጠቀም የእነሱ ደካማ ጎን ላይ እየሰራን ነው ያለነው። በአሸናፊነት ለመውጣት ጠንክረን እየሰራን ነው። ” ያሉት አሰልጣኙ ” በውድድሩ ቻምፒዮን ሆነን ለመጨረስ በአካላዊውም በአዕምሯዊም ረገድ ጠንከር አድርገን እየሰራን ነው። ከከተማ አስተዳደሩም በኩል ትልቅ ድጋፍ እና እገዛ እየተደረገልን ነው። ዝግጁ ነን ፤ አንደኛ ሆነን ለመጨረስ ጠንክረን እየሰራን ነው።” ሲሉም አክለዋል።
በእርግጥ የሊጉ በተለይ የዚህ ምድብ ቡድኖች የአቋም ወጥነት ጥያቄ የሚነሳበት ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ለገጣፎ ለገዳዲ ከመሪነቱ ባሻገር በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ ቡድን ይመስላል። በስብስቡ ውስጥ የከፍተኛ ሊግ ባህርይን የሚያውቁ ተጫዋቾች መኖራቸው ወሳኙን ወቅት በድል ለማጠናቀቅ ሊረዳቸው ይችላል። አሰልጣኝ ጥላሁንም ቡድናቸው በቅድሚያ ከፊቱ የሚጠበቀው ጨዋታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ፤ ነገር ግን ምድቡን በበላይነት ለማጠናቀቅ እንደተቃረበም ዕምነታቸውን በዚህ መልኩ አስቀምጠዋል። ” ካለን ተነሳሽነት እና ፍላጎት መነሻነት ወደ ዋንጫው እየተቃረብን ነው። ቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች ትዕግስት እና ማስተዋል ይፈልጋሉ። ባሉን ቀናቶች ውስጥ እነዚህን ነገሮች አስተካክለን እንጫወታለን። ቅድሚያ የምንሰጠው ግን ለቡራዩ ጨዋታ ነው። የቡራዩ ላይ ትኩረት አድርገን ማሸነፍ ወይንም አቻ ለእኛ ይልቅ ውጤት ነው። ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾችም አገግመው በመምጣታቸው በየቦታው ላይ ብዙ አማራጬች አሉን። የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬ አስባለሁ ከፈጣሪ ጋር።”
የለገጣፎ ለገዳዲ ያለፉት ዓመታት ሙከራ ዘንድሮም ቀጥሎ በውጤት ውጣ ውረድ የታጀበ የውድድር ዘመን አሳልፎ እዚህ ደርሷል። ቡድኑ መሪነቱን አስጠብቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ህልሙን ያሳካ ይሆን ?