ወልቂጤ ከተማ ዩጋንዳዊውን የግብ ዘብ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ለበርካታ ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ባለማስደፈር ሪከርድ የያዘው ግብ ጠባቂ ዳግም ወደ ሀገራችን በመመለስ ወልቂጤ ከተማን ሊቀላቀል ነው።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከታዩ ምርጥ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራ ነው። ከ2003 አጋማሽ እስከ 2010 ድረስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ቆይታ ያደረገው ሮበርት ኦዶንካራ ለ5 ጊዜያት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከክለቡ ጋር በተመሳሳይ አምስት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ክብርን በግሉ ማግኘቱ አይዘነጋም። ተጫዋቹ ሰባት ዓመት ከግማሽ ካገለገለበት ክለብ ከወጣ በኋላ በአንድ ዓመት ውል ወደ አዳማ ከተማ አቅንቶ ከተጫወተ በኋላ ወደ ጊኒው ሆራያ ማምራቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ሦስተኛ ክለቡ ወደሚሆነው ወልቂጤ ከተማ ለማምራት አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ ይደርሳል።

ክረምት ላይ ሠራተኞቹን ተቀላቅሎ የነበረው ሲልቫይን ግቦሆ በፊፋ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅሟል በሚል ከታገደ በኋላ ቦታውን በሰዒድ ሀብታሙ ለመሸፈን ሲጥር የነበረው ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በ16 ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ባለሪከርዱ ኦዶንካራን ማግኘቱ ለክለቡ መልካም የሚባል ዜና ነው። ተጫዋቹ ዛሬ አመሻሽ መዲናችን ከደረሰ በኋላ የቀድሞ የግብ ዘቡ ግቦሆ የወረቀት ጉዳዮች ሲገባደዱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ፊርማውን እንደሚያኖር ሰምተናል።