ለወራት የዘለቀው ውዝግብ መቋጫ አግኝቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በድሬዳዋ ከተማ እና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እልባት አግኝቷል።

በ2013 የውድድር ዘመን መሐል ላይ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን የጨረሰው ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮም ከአሰልጣኙ ጋር ለሁለት ዓመታት ለመቀጠል ተስማምቶ ውድድሩን ጀምሮ ነበር። ሆኖም የክለቡ እና የአሰልጣኙ የሥራ ግንኙነት ከዘጠነኛው ሳምንት ያለፈ አልነበረም።

የቡድኑ ውጤት እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያልተዋጠላቸው ድሬዎች አሰልጣኙን በዕግድ አቆይተው የ20 ዓመት በታች ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ውሳኔ በማሳለፍ ኃላፊነቱን ለቴክኒክ ዳይሪክተሩ ፉዓድ የሱፍ ሰጥተዋል። አሰልጣኝ ዘማሪያም ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን ኮሚቴ ከወሰዱት በኋላም ክለቡ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሯል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲካረር የቆየው የሁለቱ አካላት ግንኙነት መቋጫው ምን እንደሚሆን በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ሲጠበቅ ቆይቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አበበ ፣ ዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ፣ የድሬዳዋ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ፣ አሰልጣኝ ዘማሪያም እና የህግ አማካሪያቸው አቶ ብርሃኑ ረፋድ ላይ ውይይት አድርገው ነበር። በዚህም በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው ውዝግብ በዕርቅ እንዲፈታ መወሰኑን የህግ አማካሪ እና የእግር ኳስ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ ነግረውናል።