[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የዛሬ ፍልሚያዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት እና ላለመውረድ የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ ኢትዩ ኤሌክትሪክ ከሀላባ ከተማ ጋር 1-1 አቻ ተለያይቷል። ብዙም ማራኪ ባልነበረው ጨዋታ ቀድመው ወደግብ መድረስ የቻሉት ኤልፓዎች ነበሩ። በዚህም በ1ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ሳጥን ጠርዝ ላይ ኢብራሂም ከድር ወደ ግብ በቀጥታ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ ሲሆን ተደጋጋሚ ኳሶችን ሲያገኝ የነበረው ኢብራሂም 4ኛው ደቂቃ ላይ ጨረቃው ላይ ያገኘውን ሌላ ኳስ
በድጋሜ ወደ ግብ እክርሮ ቢመታውም ለጥቂት ወጥቶበታል።
ሀላባዎች በበኩላቸው የኤልፓዎችን ጨዋታ በማቋረጡ በኩል የተሰካ ስራ ሲሰሩ የቆዩት ሲሆን በ20ኛው ደቂቃ ላይም ያገኙትን የመጀመሪያ አጋጣሚ ሙሉቀን ተሾመ ወደግብነት ቀይሮት መመራት ጀምረዋል። ሀላባዎች በድጋሜ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሙሉቀን ተሾመ በግራ መስመር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከተመሩ በኋላ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ኤልፓዎች በ31ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ የተገኘውን ኳስ አቤል ሀብታሙ ወደ ግብ ሲመታው ግብጠባቂ አውጥቶበት የተገኘውን የመዓዘን ምት በእምነት ደምሴ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ እድሎችን ያገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 38ኛው ኢብራሂም ከድር ከአቤል ሀብታሙ የተሰነጠቀለትን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረው ግን አስቆጪ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው መጫወት የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች በመስመር ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም መስመር ተጫዋቾቻቸው የተጠበቀውን ያህል ወጤታማ መሆን አልቻሉም። በሙከራ ደረጀ ሀላባዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግስቱ በቀኝ መስመር ቀጥታ ወደግብ የመታው የቅጣት ምት ግብ ጠባቂ ያወጣበት የሚጠቀስ ነበር። በኤልፓዎች በኩል 62ኛው ደቂቃ ላይ ካርሎስ ዳምጠው በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደግብ አክርሮ ቢመታውም ኢላማውን መጠበቅ አልቸለም። የኤልፓን ጫና ተቋቁመው የሚጫወቱት ሀላባዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ጥሩ አጋጣሚ ማናዬ ፋንቱ ሳጥን ውስጥ ቢያገኘውም በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩት ሁለት ጎሎች በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
10:00 ሰዓት ላይ የተደረገው የአምቦ ከተማ እና ጌዲዮ ዲላ ጨዋታ ማራኪ የኳስ ፍሰት የታየበት ሲሆን እንቅስቃሴውም ጨዋታውን ለመታደም ስታዲየም ውስጥ የተገኘውን ደጋፊ አስደስቷል። በጨዋታውም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት አምቦ ከተማዎች ነበሩ። በዚህም በ14ኛው ደቂቃ ግዛቸው ኃይሉ ሳጥኑ ጠርዝ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታው ግብ ጠባቂው በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣው መዳረሻው በግቦቹ መሐከል የሚገኘው መረብ ነበር። የወጣውን ኳስ ተከትሎ የተገኘውን የማዓዘን ምት ራሱ ግዛቸው አስቆጥሮ አምቦ መሪ መሆን ችሏል። ዲላዎች ተጭናው በመጫዎት 34ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ አቤኔዘር ህዝቃኤል ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመልስ ሙሉዓለም በየነ በጭንቅላት በመግጨት ግብ አስቆጥሮ አቻ ሆነው ወደ እረፍት አምርተዋል።
እረፍት መልስ ጥሩ ፉክክር በነበረበት ጨዋታ ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ፍሰት እንዲሁም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በሁለቱም በኩል ተደርገዋል። በሙከራ ደረጃ ቀዳሚ የነበሩት አምቦዎች በ54ኛው ደቂቃ ጫላ ከበደ ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ነገርግን ቋሚው የመለሰበት ጥሩ አጋጠሚ ነበር። ዲላዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሰለሞን ጨርሶ ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶ የሰጠውን ኳስ ሙሉዓለም በየነ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎት መሪ መሆን ችለዋል።
ከመምራት ወደ መመራት የተሸጋገሩት አምቦዎች ጫና ፈጥራው በማጥቃት 69ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ግዛቸው ኃይሉ ወደ ግብ ቀይሮት አቻ ሆነዋል። በዲላዎች 72ኛ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቱ ሳይጠቀምበት የቀረበትን ዕድል ጨምሮ ሌሎች አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውን ሁለት አቻ ፍፃሜውን አግኝቷል። ውጤቱም ተከትሎ አምቦ ከተማ ሁለት ጨዋታዎች እየቀረው ከወዲሁ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል።