የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ተጠባቂ የ16ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚገባውን ቡድን ፍንጭ የሚሰጡት የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች በቤንች ማጂ ቡና እና በለገጣፎ ለገዳዲ አሸናፊነት ተጠናቀዋል።

08:00 ላይ ቤንች ማጂ ቡና እና ቡታጅራ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በቤንች ማጂ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተገባዷል። ጨዋታው በሁለቱም በኩል በፍጥነት ወደ ጎል በሚደረጉ ምልልሶች ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተን ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃ ነበር። የቡታጅራው አጥቂ ወንድማገኝ አብሬ በነፃ ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለውሳኔ ሲያመነታ የቤንች ማጂ ተከላካይ ከጀርባው ደርሶ ተደርቦ ያወጣት በአንፃሩ ቤንች ማጂ ቡናዎች በኩል ኤፍሬም ዓለሙ በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ የመታው እና ግብ ጠባቂው እንደምንም ያዳነበት በድጋሚ ከሳጥን ውጪ ግዙፉ ተከላካይ በዕውቀቱ ማሞ አክርሮ የመታውና ለጥቂት በግቡ አናት የወጣው በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የተፈጠሩ የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ።

በጥሩ ሙከራዎች ታጅቦ የጀመረ የሚመስለው ጨዋታ ቀዝቀዝ እያለ የመጣ ቢመስልም በ24ኛው ደቂቃ በቤንች ማጂ ቡናዎች ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ለቀኝ መስመር ባጋደለ አቅጣጫ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የሰጠውን ቅጣት ምት ጄይላን ከማል ሲያሻግረው በቁመት አጠር የሚለው የመስመር አጥቂው ዘለዓለም በየነ በግንባሩ በመጨት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ የቡታጅራው በጋሻው ክንዴ ከሳጥን ውጪ ከጎሉ ፊት ለፊት የተሰጠውን ቅጣትም በቀጥታ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራ በፍጥነት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበት አጋጣሚ ነበር።

የጨዋታው ሂደት ቀጥሎ በ45ኛው ደቂቃ የዕረፍት ሰዓት መዳረሻ ለይ ከርቀት አማካዩ ሰይድ ሰጠኝ በቀጥታ በመምታት ግሩም ጎል በማስቆጠር የቤንች ማጂ ቡናን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። በዚሁ ሂደት የቡታጅራው ግብ ጠባቂ ሚስባሀ ተዘፍልፎ በመውደቁ ህክምና እስኪያገኝ ድረስ ጨዋታውን ለማስቀጠል የተወሰነ ደቂቃ ወስዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ጨዋታውን ለመቆጣጠር የፈለጉት የቤንች ማጂ ቡናው አሰልጣኝ መሐመድ ኑር ተሳክቶላቸው በ60ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን አጥቂው ወንድማገኝ ኬራ በፍጥነት በመግባት ተረጋግቶ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን አረጋግቷል። ቤንች ማጂዎች ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ ተረጋግተው የጨዋታውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በቀሩት ደቂቃ ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃሩ ቡታጅራዎች በሚገኙ አጋጣሚዎች ወደፊት በመሄድ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ74ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ መሳይ ሰለሞን የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች የተለየ ነገር ሳያስመለክተን ጨዋታው በቤንች ማጂ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት ቤንች ማጂዎች ደረጃቸውን በማሻሻል ከመሪው በሦስት ነጥብ ዝቅ ብለው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲን ከቡራዩ ከተማ አገናኝቶ በለገጣፎ 1-0 አሸንፏል። ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ከሚመዘገበው ውጤት አኳያ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ጥንቃቄ በመምረጥ ከራሳቸው ሜዳ ሳይወጡ በሚገኙ አጋጣሚዎች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ማሰባቸው የመጀመርያው አጋማሽ እምብዛም የጠራ የጎል ሙከራዎችን አላስመለከቱንም።


ከውሃ ዕረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ወደ ፊት በመሄድ ክፍት ቦታ ለማግኘት በመፈለጋቸው ጨዋታው በሙከራ ተነቃቅቶ በ32ኛው ደቂቃ ቡራዩዎች በጫላ በንቲ አማካኝነት ከግራ መስመር ወደ ሳጥን በመግባት መሬት ለመሬት መትቶ ሰው ሳያገኝ በግቡ ቋሚ ጠርዝ የወጣው የመጀመርያው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ውጥረት ተሞልቶበት በቀጠለው ጨዋታ ለገጣፎዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል በ39ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል። ጎሉንም በአስደናቂ ሁኔታ ከሳጥን ውጭ በመምታት አንዋር አብዱልጃፋር ከመረብ ላይ አሳርፎታል።

በሁለተኛው አጋማሽ እምብዛም የጎል ሙከራ ያልተመለከትንበት ሆኖ ሲቀጥል የጨዋታው መጠናቀቂያ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ቡራዩዎች ጫና ፈጥረው የአቻነት ጎል ፍለጋ በቴድሮዎስ ታዳሰ እና ጴጥሮስ ገዛኸኝ አማካኝነት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመጨረሻም ለገጣፎዎች በልደቱ ለማ እና በፋሲል አስማማው አማካኝነት ጨዋታውን መግደል የሚችሉበት ያለቀለት ኳስ አግኝተው ሳይጠቀሙ ተጠባቂው ጨዋታ በለገጣፎ ለገዳዲ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል። ከአንደኛ ሊግ ካደገበት ዓመት ጀምሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ ሲተጋ የቆየው ለገጣፎ ውጤቱን ተከትሎ ምድቡን በሦስት ነጥብ እንዲመራ አስችሎታል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የቡራዩው ግብ ጠባቂ አይችሉም ብርሀኑ የውድድሩን ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ምህረትአየውን ለመደብደብ የተጋበዘበት መንገድ ትኩረትን የሳበ ነበር።

ያጋሩ