የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 16ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥሎ መድን መሪነቱን ያጠናከረበትን ወሳኝ ድል ሲያሳካ ፌዴራል ፖሊስ የካ ክፍለ ከተማን እየመራ ያለበት ጨዋታ ተቋርጧል።

8፡00 ላይ ጉኡሌን የገጠመው መድን 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክር ያስመለከተን እና ፋታ የለሽ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በርከት ብለው ባየንበት የሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች የኢትዮጵያ መድን እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ገና በጊዜ ሳቢነቱ ጀምሯል። በተለይ የመጀመሪያዎቹን አምስት ደቂቃዎች ኳስ በመቆጣጠር በተጋጣሚ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ጉለሌዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ወደ መስመር ባደላ የጨዋታ መንገድ ለመጫወት የሞከሩት መድኖች በተደጋጋሚ የጉለሌ የግብ ክልል ሲደርሱ ተመልክተናል፡፡

መድን መሐል ሜዳ ላይ በበኃይሉ ሀይለማርያም እና ቢኒያም ካሳሁን እንዲሁም መስመር ላይ ያሬድ ዳርዛ እና ልዩነት ፈጣሪ በነበረው ኪቲካ ጀማ ላይ ያተኮረ አጨዋወት ሲከተሉ ነበር፡፡ በዚህ የጨዋታ ሂደትም ኪቲካ ጀማ ሦስት ያለቀላቸውን ዕድሎች ፈጥሯል፡፡ በ15ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል በኃይሉ ከዳግም ሰለሞን ጋር በፈጠረው ድንቅ ቅንጅት ለኪቲካ ሰጥተውት ተጫዋቹ መረጋጋት ባለመቻሉ በቀላሉ ያመከናት ኳስ ምን አልባት ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች፡፡

ቀስ በቀስ የመድን ተከላካዮች የሚሰሩትን ስህተት እየጠበቁ ጥቃት ለመሰንዘር ሲታትሩ የነበሩት ጉለሌዎች መሀመድ ንዳ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ ያመከነበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው። መድኖች በተደጋጋሚ ግብ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት 38ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡ በዚህም ኪቲካ በግል ጥረቱ የፈጠረውን የግብ ማግባት ዕድል ቢኒያም ካሳሁን ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ተጨራርፋ ሲመለስ ራሱ ኪቲካ ደርሶበት ከመረብ አሳርፎ ቡድኑ ቀዳሚ ሆኗል፡፡

በመድን 1ለ0 በሆነ ውጤት የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ ጉለሌዎች የተሻሉ ሆነው መታየት የቻሉበት ቢሆንም የግብ ዕድሎች በጠራ መልኩ በማድረጉ ረገድ የአሰልጣኝ በፀሎቱ መድን ሻል ብሎ ቀርቧል፡፡ ገና አጋማሹ በተጀመረ ሰከንዶች ውስጥ ኪቲካ ከግብ ጠባቂው ፓላክ ቾል ጋር ተገናኝቶ በተመለሰበት አጋጣሚ ጥቃት ወደ መሰንዘሩ በጊዜ ገብተዋል፡፡ ኳስ በመቆጣጠር ብርቱ ትግል ጉለሌዎች ሲያስመለክቱን ቢውሉም ወደ ጎል ደርሶ ልዩነት በመፍጠሩ ረገድ ግን እጅጉን ደካሞች ነበሩ፡፡ በአንፃሩ ፋታ ሳይሰጡ በፈጣን ሽግግር ሲጫወቱ የታዩት መድኖች በያሬድ ዳርዛ፣ ኪቲካ ጀማ እና ቢኒያም ካሳሁን አማካኝነት ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

ያሬድ ግልፅ የማግባት አጋጣሚን ያመከነበት እና ኪቲካ አገባው ሲባል በግብ ጠባቂ የተመለሰበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ፍሬ የሆነው ቢኒያም ካሳሁን ከሳጥን ጠርዝ መትቶ ሊመለስ የቻለበት ሂደት አስቆጪዎቹ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ እዮብ ገብረማርያም እና አብዱለጢፍ ሙራድ የፈጠሩለትን ዕድል ተጠቅሞ ሀይከን ድዋሙ ያገኛት ኳስ ወደ ጎል በመለወጥ መድንን 2ለ0 አሸናፊ በማድረግ ቡድኑ ከነቀምት ያለውን ነጥብ ልዩነት በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ አራት ማሳደግ እንዲችል አድርጓል።

10፡00 ሲል የዚህ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ጀምሯል፡፡ አጀማመሩ ቀዝቀዝ ባለ አየር ነገር ግን ደቂቃዎች ሲገፉ ጠንከር ባለ ንፋስ እና ዝናብ የታጀበው የፌዴራል ፖሊስ እና የካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ መልካም የሚባል ፉክክርን አሳይቶናል፡፡ በመጀሪያው አጋማሽ ገና የዳኛው ፊሽካ እንደተሰማ እሱባለው ፍቅሬ ከሳጥኑ ጠርዝ በቅብብሎሽ ሂደት ያገኘውን ዕድል በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታ በላይኛው የግቡ አግዳሚ ብረት የተመለሰበት ሙከራ በጊዜ የታየ ነበር። ጨዋታው 19ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ሊቋረጥ ግድ ብሏል። በተጠቀሰው ደቂቃ በሀዋሳ በጣለው ከባድ ዝናብ እና አደገኛ ንፋስ የተነሳ ጨዋታው ለ55 ያህል ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል። የጣለው ዝናብ እና ንፋስ ከተባለው ደቂቃ በኋላ ረገብ እንዳለ የዕለቱ ዳኞች እና የሁለቱ ክለብ አካላት እንዲቀጥል በተስማሙት መሠረት ጨዋታው ዳግሞ ተጀምሯል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች እጅግ የሚማርክ የሜዳ ላይ አቅምን ሲያሳዩን የነበሩት ፌዴራል ፖሊሶች በፈጠሩት ፍሰት ያለው እንቅስቃሴ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡ 31ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት እያሱ ከተከላካዮች መሀል ያገኘውኝ ኳስ አፈትልኮ ወጥቶ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጎሏ ስትቆጠር ከጨዋታ ውጪ ነበረች በሚል የየካ የቡድን አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ በረዳት ዳኛው ላይ ሲያሰሙ አስተውለናል፡፡ ጨዋታው ቀጥሎ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የየካው ተከላካይ ዘላለም በረከት በእሱባለው ፍቅሬ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ እሱባለው ከመረብ አዋህዶ የጎል መጠኑን ወደ ሁለት አሳድጓል፡፡ የካዎች በተቃራኒ ከማዕዘን ምት ዘላለም በረከት ካደረጋት ብቸኛ ሙከራ ውጪ የጠራ አጋጣሚን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ 40ኛው ደቂቃ ላይ ፌዴራል ፖሊሶች በእሱባለው ፍቅሬ ግሩም ጎል 3ለ0 እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡

ጨዋታው ከእረፍት በኋላ ግን ሊቀጥል አልቻለም። ምንም እንኳን ዝናብ እና ንፋሱ ቢቆሙም ሰዓቱ እየመሸ መጥቶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ፓውዛ ዝግጁ አለመሆኑን ተከትሎ ቀሪው አርባ አምስት ደቂቃ ነገ ረፋድ 4፡00 ሰአት እንዲቀጥል ቀጠሮ ተይዞ ተጠናቋል።

ያጋሩ