ከነገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በፊት የኮሞሮስ ተጫዋቾች ሀሳብ ሰጥተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

👉”ለቀልድ ስላልሆነ የተሰባሰብነው ጨዋታውን በትኩረት እንቀርባለን” መሐመድ የሱፍ


👉”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ተከታትለናል” ቻከር አልሀዱር

የዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች የጨዋታ ወቅት በዛሬው ዕለት የተከፈተ ሲሆን በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉት የኢትዮጵያ እና ኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድኖች በነገው ዕለት በማሉዚኒ ስታዲየም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ በመያዝ እየተሰናዱ ይገኛል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በትናንትናው ዕለት 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ስፍራው አቅንቷል።

ጨዋታውን በሜዳዋ የምታደርገው ኮሞሮስ ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ ቡድኗን በአዲስ መልክ ለመገንባት የምታደርገውን ጉዞ “ሀ” ብላ የምትጀምርበትን ፍልሚያ በጉጉት እየጠበቀች ትገኛለች። የ48 ዓመቱን ፍራንኮ-ሞሮኳን አሠልጣኝ ዩነስ ዜርዱክን ከሳምንታት በፊት የቀጠረው ቡድኑም 24 ተጫዋቾችን በመጥራት በሳምንቱ መጀመሪያ ልምምዱን ሞሮኒ ላይ ቢጀምርም የተሟላ ስብስቡን ያገኘው በትናንትናው ዕለት ነበር።

ከወዲሁ ለ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዝግጅታቸውን ለመጀመር ያሰቡት ኮሞሮሶች ትናንት በማሉዚኒ ስታዲየም ልምምዳቸውን ለህዝብ ክፍት አድርገው ሲሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በስታዲየም ተገኝተው እንዳበረታቷቸው ተገልጿል። ልምድ ያለው የቡድኑ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው እና ብዙዎቻችን በአፍሪካ ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ቡድኑ በኮቪድ-19 ምክንያት የግብ ዘቦቹን ሲያጣ ቦታውን ሸፍኖ ሲጫወት ተምናስታውሰው ቻከር አልሀዱር ነገ የሚደረገውን ጨዋታ አስመልክቶ ተከታዩን አጭር ሀሳብ አጋርቷል።

“የነገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው። በአዲስ አሠልጣኝ እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ቡድኑ ሽግግር ላይ ነው። ስለዚህ ጨዋታውን በደንብ ትኩረት ሰጥተን ነው የምንጫወተው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ተከታትለናል። በጣም ጥሩ ቡድን እና ፈጣን አጨዋወት የሚከተል ቡድን ነው።” ሲል የቡድን አጋሩ መሐመድ የሱፍ ደግሞ “ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን አስባለው። ለቀልድ ስላልሆነ የተሰባሰብነው ጨዋታውን በትኩረት እንቀርባለን።” በማለት ንግግሩን አሰምቷል።

እንደገለፅነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወደ ስፍራው ትናንት ቢያመራም ከጨዋታው በፊት የቅድመ ጨዋታ መግለጫ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሰናጅነት ባለመዘጋጀቱ በቡድኑ በኩል ያለውን ሀሳብ ማድመጥ አልቻልንም።

ያጋሩ