አርባምንጭ ከተማ ከመስመር አጥቂው ጋር ተለያይቷል

በቅርቡ አንድ አጥቂ ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት አዞዎቹ ከመስመር አጥቂያቸው ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።

ለሁለተኛው ዙር ቅድመ ዝግጅታቸውን በመቀመጫ ከተማቸው ከጀመሩ የሰነባበቱት አርባምንጭ ከተማዎች ራሳቸውን ለማጠናከር ወደ ዝውውሩ በመግባት አህመድ ሁሴንን ከወልቂጤ ከተማ ማስፈረማቸው ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ከመስመር አጥቂያቸው ራምኬል ሎክ ጋር በስምምነት መለያየታቸው ተረጋግጧል። ለመለያየታቸው ምክንያት ራምኬል ለክለቡ ባስገባው የመልቀቂያ ጥያቄ መሠረት ሲሆን ክለቡም ጥያቄውን ተቀብሎ መልቀቂያ በመስጠት ተጫዋቹን ሸኝቶታል።

አርባምንጭ ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲመለስ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ራምኬል በመጀመሪያው ዙር ውድድር ለ218 ደቂቃዎች ብቻ ለክለቡ ግልጋሎት ሰጥቷል። ከዚህ ቀደም ለንግድ ባንክ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለፋሲል ከነማ፣ ለድሬደዋ ከተማ እና ለወልዋሎ ዓ/ዩ የተጫወተው ተጫዋቹ በቅርቡም ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ ያመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ያጋሩ