በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ስሙ በአሉታዊ ጎኑ እየተነሳ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በዛሬው ዕለት የተላለፈበት ውሳኔን እስኪፈፅም በዝውውር መስኮቱ መሳተፍ አይችልም።
በቀድሞ ተጫዋቾቹ እና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ክሶች የበረከቱበት ሀዲያ ሆሳዕና በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፍትህ አካላት እና መደበኛ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ሲወሰኑበት እንደነበረ ይታወሳል። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ደግሞ በቀድሞ አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለ አማካኝነት የደረሰበትን ክስ ተከትሎ የተወሰነበትን ውሳኔ በጊዜ ገደቡ ተግባራዊ ባለማድረጉ ዕግድ ተላልፎበታል።
ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ለአሠልጣኙ ያልተከፈላቸው ደሞዝ ይከፈላቸው ብሎ ቢወስንም ክለቡ ይግባኝ ጠይቆ እንደነበር ይታወሳል። የክለቡ ይግባኝም በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውድቅ ሆኖ ውሳኔው ቢፀናም አመልካች (አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ) ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ውሳኔው አልተፈፀመልኝም በማለት ዳግም ለፌዴሬሽኑ አቤቱታ አቅርበዋል።
የአሠልጣኙን ጉዳይ በሕግ አማካሪነት ሲከታተሉ የቆዩት አቶ ብርሐኑ በጋሻው ባደረሱን መረጃ መሰረት ክለቡ የዲሲፕሊን ውሳኔን ተግባራዊ ባለማድረጉ ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት የስራ አገልግሎት እንዳያገኝ እና የተጫዋች ዝውውር አገልግሎት እንዳያገኝ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።