“በቶሎ ወደ አሸናፊነት መንፈስ ለመመለስ ትኩረት አድርገን ሰርተናል” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከወሳኙ የመልስ ጨዋታ በፊት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል መግለጫ ሰጥተዋል።

በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ በማጣሪያ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የደርሶ መልስ ጨዋታው ላይ ደርሷል። ከጋና አቻው ጋር በሜዳው ቀዳሚውን ጨዋታ አድርጎ 3-0 የተሸነፈው ብሔራዊ ቡድኑ የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ነገ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የሚያቀና ሲሆን ጨዋታውም የፊታችን እሁድ ይከናወናል።

ዛሬ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዱን ያደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የመልሱን ጨዋታ እና የእስካሁኑ ዝግጅታቸውን የተመለከተ መግለጫ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሰጥተዋል። ቡድናቸው በቀን አንዴ በጊዮርጊስ እና በ 35 ሜዳ ላለፉት 13 ቀናት መልካም የዝግጅት ጊዜ እንደነበረው የገለፁት አሰልጣኙ በሚፈልጉት ልክ ለመዘጋጀት የሰሞኑን ዝናባማ የአየር ሁኔታን ተከትሎ የሜዳዎች መጨቅየት ዕክል እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው የ3-0ውን ሽንፈት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ደግሞ “ሽንፈቱ ብዙ ነገሮችን እንድናስብ እና እንድንሰራ አድርጎናል። እንደቡድን እንዲህ ዓይነት ሽንፈት ሲመጣ ቶሎ መነሳት እንጂ መተኛት ተገቢ አይደለም። ትልልቅ ብሔራዊ ቡድኖችም ጎሎች ተቆጥሮባቸው ሊሸነፉ ይችላሉ። በቶሎ ወደ አሸናፊነት መንፈስ ለመመለስ ትኩረት አድርገን ሰርተናል።” ብለዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሲስጡ በመጀመሪያው ጨዋታ ቀዳሚ አጋማሽ በበድኑ ላይ የታየውን አለመረጋጋት በሴቶች እግርኳስ (በሊጉ ላይ) ባልተለመደ ሁኔታ በጋናው ጨዋታ የተመልካች ቁጥር መበራከቱ እንደድጋፍ የሚወሰድ ቢሆንም ለተጫዋቾች አዲስ መሆኑ ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው እንደሚያምኑ ገልፀው ግቦች የተቆጠሩት ግን በተሰሩ ስህተቶች መነሻነት እንደነበር አስምረውበታል። እንደቡድን ተደራጅቶ ካለመጫወት መነሻነት ጋናዎች የገኙትን አጋጣሚ መጠቀማቸው እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻሉ ዕድሎችን ፈጥሮ እንደነበርም አንስተዋል።

ከጋና የአየር ንብረት ጋር በተመሳሰለ ቦታ ላይ ቡድኑ ልምምዱን አለማድረጉ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ ተጠይቀውም ያንን ማድረግ የተሻለ ይሆን እንደነበር ሆኖም የቦታ ለውጥ ሳይደረግ በፀሀያማ ሰዓቶች ላይ ልምምዶችን ለመከወን አቅደው ወቅታዊው የዓየር ሁኔታ እንዳላሳካላቸው ተናግረዋል። ከአየር ንብረት ልዩነት ባለፈ ከውጤቱ መስፋት ጋር በተያያዘ በእግርኳስ ከባባድ ውጤቶች እንደሚቀለበሱ ለማሳየት ይህ እውነት የታየባቸው የቅርብ ዓመታት የአውሮፓ ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ተጨዋቾቻቸውን ለማነሳሳት መሞከራቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

በማስከተል የተነሳው የተጨዋቾች ዕድሜ ተገቢነትን እና ለ20 ዓመት በታች ውድድር ሊጉ መቋረጡን የተመለከቱት ጥያቄዎች ግን አሰልጣኙን ደስተኛ ያደረጉ አልነበሩም። “እኔ የላብራቶሪ ሰራተኛ አይደለሁም” በማለት መልስ መስጠት የጀመሩት አሰልጣኝ ፍሬው ውድድር እና ደንብ የራሱ የሆነ አካሄድ እንዳለው በማንሳት “በህግ አምናለው ህግ ያመጣቸውን ተጫዋቾች አስተናግዳለሁ።” በማለት ተጫዋቾቻቸው ካፍ የሚፈቅደውን የዕድሜ ክልል እስካሟሉ ድረስ መሰል ጥያቄዎች በእርሳቸው መቅረብ እንደማይገባቸው አብራርተዋል።

ከውድድሩ መቋረጥ ጋር በተያያዘም አሰልጣኙ “የወንዶቹ ብሔራዊ ቡድንም ለአፍሪካ ዋንጫ ሲሄድ ውድድር ቆሟል። ምንድነው ልዩነቱ ? እኛ ጋር የመጣው አዲስ ነገር ምንድነው ?” ብለው በመጠየቅ “ይሄ ውድድር አይደለም ሌላም ተዘግቶ የኢትዮጵያ እግርኳስ ውጤት ማምጣት ከቻለ ውጤቱ ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን። የክለቦች ግብዓት መምጣት ያለበት ለብሔራዊ ቡድን ነው። መታወቅ ያለበት ያ ነው። ውድድሩ የተዘጋው ውጤታማ ቡድን ስለሆነ ነው ለሌላ አይደለም።” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ ውጪ በመግለጫው ላይ አሰልጣኙ አሁንም ለተጋጣሚያቸው ተገቢውን ክብር እንደሚሰጡ ጠቅሰው በስብስባቸው ውስጥ በህመም ላይ በመሆኗ የማትሰለፈው ረድዔት አስረሳኸኝ አለመኖር ቡድናቸው በአንድ ሰው ላይ የልተሰራ እና እንደቡድን የተገነባ በመሆኑ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር አስረድተዋል።