ዕድሉ ደረጄ የአውሮፓ ‘ሲ’ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ሥልጠናን ለመውሰድ ዛሬ ወደ ናሚቢያ አቅንቷል።
በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ያሳካውን ስኬት በአሰልጣኝነቱም ለመድገም እየተጋ የሚገኘው ዕድሉ ደረጄ የአሰልጣኞች ሥልጠናን በሀገር ውስጥ እና በውጪ የወሰደ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በነበረው ዘገባችን ስኮትላንድ ከሚገኘው One 10 sport ኮሌጅ ጋር የአውሮፓ ‘ሲ’ ላይሰንስን ለመውሰድ የንድፈ ሀሳብ ትምህርቱን በኦላይን መከታተሉን ገልፀን ነበር።
ሆኖም የኮቪድ ወረርሺኝ በዓለም ላይ መከሰቱን ተከትሎ የተግባር ላይ ትምህርቱን ሳይወስድ ሊቋረጥ ችሏል። አሁን ነገሮች የተስተካከሉ መሆናቸውን እና ዩኤፋ የቀረውን የተግባር ላይ ትምህርቱን ለመስጠት ማሰቡን ተከትሎ ቀሪውን ትምህርቱን ለመከታል እና ፈተናውን ለመውሰድ ዛሬ ወደ ሥፍራው አቅንቷል።
ሥልጠናው የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ከናሚቢያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አፍሪካውያን አሰልጣኞች የአውሮፓ ‘ሲ’ ላይሰንስን እንዲወስዱ በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ 84 ሰልጣኞች የሚሳተፉበት እና ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ ሥልጠና ላይ ዕድሉ ትምህርቱን በብቃት ካጠናቀቀ የአውሮፓ ሲ ላይሰንስን የሚያገኝ ይሆናል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያለፈው ዕደሉ ወደ ሥልጠናው በመግባት የተለያዩ ክለቦችን አሰልጥኖ ያለፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ20 ዓመት በታች የንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። የቀድሞው ተጫዋች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ድግሪ ያለው ሲሆን በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በስፖርት ማኔጅመትን ማስተርሱን በቅርቡ መያዙ ይታወቃል።