[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው አዳማ ከተማ ከዩናይትድ ቤቭሬጅስ ጋር የአምስት ዓመት የአጋርነት ስምምነት በዛሬው ዕለት ፈፅሟል።
ከረፋዱ 5 ሰዓት ጀምሮ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በተደረገው የስምምነት መርሐ-ግብር ላይ ዩናይትድ ቤቭሬጅስን ወክለው ስራ አስኪያጁ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ፣ ሴልስ እና ዲስትሪቢውሽን ዳይሬክተሩ አቶ ኤፍሬም ትዕዛዙ፣ የሕግ እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ የኔሰው ድረስ ሲገኙ በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሙአታ አብደላ፣ ሥራ አስኪያጁ አቶ አንበስ መገርሳ፣ የክለቡ የህግ አማካሪ አቶ ብርሃኑ በጋሻው እንዲሁም ዋና አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ እና አምበሉ ጀማል ጣሰው በመድረኩ ተሰይመዋል።
ዝግጅቱ በሀገር አባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን በቅድሚያም አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ ተቋማቸውን በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ካስተዋወቁ በኋላ ከአዳማ ከተማ ጋር ለመስራት ያሰቡበትን ምክንያት በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። አቶ የኔሰው ደግሞ መድረኩን ተረክበው የስምምነቱን ዝርዝር ይዘት ማስረዳት ይዘዋል። ለ5 ዓመታት በጥሬ ብር እና በአይነት በድምሩ 60 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ስምምነት የተለያዩ መዘርዝሮች ያሉት ሲሆን በጥሬ ገንዘብ ክለቡ በቀጥታ በየዓመቱ 4 ሚሊዮን ብር እንደሚያገኝ ገልፀዋል። 36 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ በአይነት መልክ እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
ከአይነት ድጋፉ መካከል በየዓመቱ ጥራታቸውን የጠበቁ 15 ሺ የደጋፊዎች መለያ ከውጪ ሀገር ተሰርቶ የሚቀርብ ሲሆን መለያው ተሸጦ የሚገኘውም ገቢ ወደ ክለቡ ካዝና እንደሚያመራ ተብራርቷል። ከደጋፊዎች ጋር ተያይዞም የተቀናጀ የመረጃ መመዝገቢያ ቋት (Data base system) እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያለው የደጋፊዎች መታወቂያ ካርድ እንደሚዘጋጅ ተመላክቷል።
ክለቡ የፋይናንስ አቅሙን ከማሳደግ በተጨማሪ በቋሚነት ገንዘብ የሚያመነጭበትን ዘዴ እንዲቀየስ አልፎም ዋናውን የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን ጨምሮ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የማሳደግ ስራም እንደሚሰራ ተነግሯል። በዋናነት ደግሞ ዩናይትድ ቤቭሬጅስ ክለቡን ስፖንሰር ያደረገው አዲሱ ዋሊን ምርቱ በአዳማ ከተማ በሚሸጥበት ወቅት በሳጥን 7 ብር ከ20 ሳንቲም ለስፖርት ልማት ፕሮጀክት እንደሚውል እንደሚያደርግ ታውቋል።
የድርጅቱ ምርትም (ዋሊን ቢራ) በዋና ዋና ትጥቆች ላይ እንደሚኖር እና ህግ በሚፈቅደው ምልኩ በስታዲየም እና ተያያዥ ቦታዎች እንደሚቀመጥ በመግለጫው ተነግሯል። የክለቡ ፕሬዝዳንት ሙአት አብደላ አስከትለው እንደ ዓምናው አይነት የመውረድ ችግሮች ዳግም እንዳይመጣ የፋይናንስ ክፍተት ትልቅ ቦታ ስላለው ይህ ስምምነት ትልቅ ችግር እንደሚቀርፍ ሲናገሩ ተደምጧል። ዋና አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ እና አምበሉ ጀማል ጣሰውም መሰል የአጋርነት ስምምነቶች ቡድናቸው በፋይናንስ እንዲጠናከር እንደሚያደርግ እና ይህ ደግሞ ለእነሱ መነሳሻ እንደሆነ ተናግረዋል።
መርሐ-ግብሩ እንዳለቀ በሰራነው ዘገባም የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ለነበረው እና በአሁኑ ሰዓት በህይወት የማይገኘው ሞገስ ታደሠን ቤተሰብ በፋይናንስ ለማገዝ ዩናይትድ ቤቭሬጅስ የ100 ሺ ብር ድጋፍ አበርክቷል። በመጨረሻም ዩናይትድ ቤቭሬጅስት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ እና የአዳማ ክለብ ፕሬዝዳንት ስምምነቱን በፊርማቸው ካፀኑ በኋላ የዩናይትድ ቤቭሬጅስ ሴልስ እና ዲስትሪቢውሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ትዕዛዙ እና የክለቡ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አዲሱን የክለቡን መለያ ተረካክበዋል።