[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
እጅግ ተጠባቂ የነበሩት የዛሬ የምድብ ለ ሦስት ጨዋታዎች የምድቡን ተፎካካሪዎች ቁጥር ከሦስት ወደ ሁለት ከመቀነስ ባለፈ አላፊውን ሳያሳውቁ ተጠናቀዋል።
ቡታጅራ የቡራዩን ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ዕድል አምክኗል
ረፋድ 04:00 ላይ ጅማሮውን ባደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የማለፍ ተስፋን ይዞ ጨዋታውን ያደረገው ቡራዩ ከተማ በሙሉ ጨዋታው ብልጫ የነበረው ቢሆንም ሳይጠበቅ በጠባብ ውጤት ሽንፈት አስተናግዶ የማለፍ ተስፋውን አጨልሟል።
ፈጥን ያለ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ቡራዩ ከተማዎች ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ባይችሉም የጨዋታ እንቅስቃሴው በቡታጅራ የሜዳ አጋማሽ ላይ እንዲካሄድ ማድረግ ችለዋል። በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ከሚደረጉ ምቶች ሌላ ዕድሎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በጨዋታው በቡራዩዎች በኩል ጨዋታውን በግራ እና ቀኝ የመስመር አጥቂነት የጀመሩት ሀብታሙ ወርቁ እና ጫላ ቤንቲ ከመስመር መነሻቸውን በማድረግ አደጋ ለመፍጠር ቢጥሩም ከቡድን አጋሮቻቸው በቂ ድጋፍ ማግኘት አለመቻላቸውን ተከትሎ ጥረታቸው መና ሲቀር አስተውለናል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በብልጫ መጫወታቸውን የቀጠሉት ቡራዩዎች በ54ኛው ደቂቃ ቶሎሳ ንጉሴ ከቀኝ መስመር ካሻገረው ኳስ መነሻነት ቴዎድሮስ ታደሰ በግንባሩ የሞከራት እና ከቅፅበቶች በኋላ ቴዎድሮስ አሻምቶለት ቶሎሳ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
በጨዋታው በተለይም መሀል ሜዳ ላይ ፍፁም የሆነ የበላይነት የተወሰደባቸው ቡታጅራዎች በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ወቅት የነበራቸው ዝግጁነት ደካማ የነበረ ሲሆን የቡራዩ ሳጥን የደረሱባቸው አጋጣሚዎች በጨዋታው በጣም ውስን ነበሩ።
የጨዋታ ደቂቃው እየገፋ መሄዱን ተከትሎ በተጋጣሚ አጋማሽ የማጥቃት ሀሳብ ዕጥረት የነበረባቸው ቡታጅራዎች ቡራዩዎች በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት በሚሞክሩበት ወቅት በ78ኛው ደቂቃ ላይ በድንገት በረጅም ኳስ ከተከላካይ ጀርባ አምልጠው በመግባት በፀጋ ማቲዎስ አማካኝነት ወደ ግብ የሞከሩት ኳስ በግብ ጠባቂው ሲመለስ ሳጥን ውስጥ የነበረው የቡድን አጋሩ እንዳለማው ታደሰ ዳግም ወደ ግብ የሞከራት ኳስ በቡራዮ ተጫዋቾች በእጅ በመነካቱ የተነሳ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ እንዳለማው ታደሰ አስቆጥሮ ሳይጠበቅ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
በቀሩት ደቂቃዎች ቡራዩዎች የማጥቃት ፍላጎት ቢኖራቸውም እንደቀደሙት ደቂቃዎች ሁሉ ውጤታማ መሆን የተሳናቸው ሲሆን በአንፃሩ ቡታጅራዎች ጨዋታውን በማቀዝቀዝ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።
በውጤቱም ቡራዩ ከተማ በ28 ነጥብ ላይ ሲገኝ ወደ ሊጉ የማደግ ተስፋው ሙሉ ለሙሉ ተሟጧል።
ካፋ ቡና በሊጉ መቆየቱ ሲረጋገጥ ቤንች ማጂ ቡና በላይኛው ፉክክር ቀጥሏል
በዕለቱ ሁለተኛ በነበረው እና ቀትር ላይ በተካሄደው ጨዋታ በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ ወሳኝነት በነበረው ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡናዎች በመጨረሻ ደቂቃ በተገኘች ግብ አቻ ተለያይተው ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመግባት ህልማቸው አስቀጥለዋል።
ገና ከጅምሩ ኳሱን ተቆጣጥረው ለማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ካፋ ቡናዎች በ7ኛው ደቂቃ ነበር መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር የቻሉት። ካፋ ቡናዎች ከመሀል ሜዳ ከቤንች ማጂ ተከላካዮች ጀርባ በረጅሙ የላኩትን ኳስ ለመቆጣጠር ግቡን ለቆ የወጣው የቤንች ማጂው ግብ ጠባቂ ፋሪስ ዓለዊ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን ኳሱን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት ወቅት የሰራውን ስህተት ተከትሎ ተስፋ ሳይቆርጥ ኳሷን የተከተለው ክንፈ መኮንን ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ቤንች ማጂ ቡናዎች በ11ኛው ሀብታሙ ረጋሳ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ፣ በ22ኛው ደቂቃ አምበላቸው ወንድማገኝ ኬራ ከሳጥን ውስጥ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ታምሩ በቀጥታ ከቆመ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ አጋማሹን በብልጫ ያጠናቀቁት ቤንች ማጂዎች ካደረጓቸው በርካታ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።
በቤንች ማጂዎች በተወሰደባቸው ብልጫ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመከላከል ለመጫወት የተገደዱት ካፋዎች በጥቂት አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት በተለይም ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ተነጥሎ ይቆም በነበረው ክንፈ መኮንን አማካኝነት ሁለት እንዲሁም በሱራፌል ፍቃዱ የግል ጥረት አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
ወደ ሊጉ የመግባት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሙሉ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸው የነበሩት ቤንች ማጂዎች አጋማሹን ፍፁም ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ በአንፃሩ ላለመውረድ ነጥቡን ይፈልጉት የነበሩት ካፋዎች ደግሞ በአጋማሹ ከጅምሩ ከአጥቂያቸው ይበልጣል አደመ በስተቀር ያሉት የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ሜዳቸው ሸሽተው ሲከላከሉ አስተውለናል።
የካፋ ቡና ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጥፋት ተሰርቶብናል በሚል መውደቃቸውን ተከትሎ እየተቆራረጠ በቀጠለው ጨዋታ ቤንች ማጂዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቡት አማካዩ ተስሎች ሳይመን ወደ ሜዳ ከገባ ወዲህ ከጥልቀት በመነሳት ዘግይቶ ወደ ሳጥን በመድረስ የሚሻሙ ኳሶችን ለመግጨትም ሆነ ኳሶችን በቀጥታ ወደ ግብ ለማድረስ ያደረገው ጥረት ለቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ በተወሰነ መልኩ ተጨማሪ አቅምን ቢፈጥርም የካፋ ቡና መከላከል ግን የሚቀመስ አልሆነም።
መደበኛው ደቂቃ መጠናቀቁን ተከትሎ የተሰጠው ተጨማሪ ሰባት ደቂቃ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ተስሎች ሳይመን ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ በማስቀቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
በጨዋታው መሪው ላይ ይበልጥ ጫና ሊያሳድሩበት የሚችሉበትን ዕድል መጠቀም ያልቻሉት ቤንች ማጂ ቡናዎች አሁንም ቢሆን ወደ ሊጉ የመግባት ዕድላቸው ያልተሟጠጠ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ ለገጣፎ የሚሸነፍ ከሆነ እና እነሱ ከሁለት የበለጠ ግብ አስቆጥረው ማሸነፍ ከቻሉ ህልማቸውን ማሳካት የሚችሉ ሲሆን በአንፃሩ ካፋ ቡናዎች ደግሞ በሊጉ የመቆየታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል።
ለገጣፎ ለገዳዲ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን የሚያረጋግጥበትን ጨዋታ አሳልፏል
ተከታያቸው ቤንች ማጂ ቡና ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በጨዋታው ባለድል መሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳልፋቸው የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከሊጉ አስቀድሞ መውረዱን ካረጋገጠው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ከጠንካራ ፈተና በኋላ አቻ ተለያይተው ወደ ሊጉ ለመግባት ቀጣዩን ጨዋታ ለመጠበቅ ተገደዋል።
በጨዋታው መውረዳቸውን ያረጋገጡት እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ በነበረው ዘላለም ፀጋዬ የሚመሩት ቂርቆስ ክፍለ ከተማዎች እጅግ ለዓይን የሚማርክ የቅብብል እግርኳስን ያስመለከቱን ቢሆንም ኳሶችን አደጋ ወደ ሚፈጥረው የሜዳ ክፍል በማሳደግ ረገድ ግን ተቸግረው ተስተውለዋል።
በአንፃሩ ለገጣፎዎች በ10ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ወንድሙ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ካደረጋት እና ዳግም አራጌ በግሩም ቅልጥፍና ካደነበት ኳስ ውጪ የቂርቆስ ቅብብሎችን በማቋረጥ በፍጥነት ወደ ግብ መሸጋገር ይመስል የነበረው የጨዋታ ዕቅዳቸው ብዙም ውጤታማ አልነበረም።
በሁለተኛው አጋማሽም የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመሳሳይ ይዘት በነበረው ጨዋታ ለገጣፎዎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር ተቸግረው የተስተዋለ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ አጨቃጫቂ በነበረ መንገድ ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ፍፁም ቅጣት ምቱንም ልደቱ ለማ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ ተገቢ አይደለም በሚል ቂርቆሶች ክስ አስይዘው በቀጠለው ጨዋታ በ63ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ የቂርቆስ ተጫዋች በለገጣፎ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ጅብሪል ናስር በተረጋጋ ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ተጋግሎ በቀጠለው ጨዋታ ቂርቆሶች በተወሰነ መልኩ ጨዋታቸው ላይ ቀጥተኝነትን ጨምረው ለመጫወት መሞከራቸውን ተከትሎ ጨዋታው ምልልሶች የበዙበት ሆኖ ሲቀጥል በዚህም ለገጣፎዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ደጋግመው የቂርቆስን የግብ ክልል መጎብኘት ጀምረዋል። ከእንቅስቃሴ ይልቅም በዚሁ አጋማሽ ተደጋጋሚ አደገኛ ዕድሎችን ከቆመ ኳስ መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ነጥባቸውን ወደ 33 በማሳደግ ከተከታያቸው ቤንች ማጂ ቡና በሦስት ነጥብ ልዩነት መምራታቸውን ሲቀጥሉ በሂሳባዊ ስሌት መሰረት ወደ ሊጉ ለመቀላቀል የመጨረሻውን ጨዋታ ለመጠበቅ ተገደዋል።