[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት በዛሬው ዕለት ተደርጓል፡፡
በዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ አስራ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት ክለቡ ባዘጋጀው መርሐ-ግብር የማበረታቻ ሽልማት እና የዕራት ግብዣ ፕሮግራም አመሻሽ ላይ በሳውዝ ስታር ሀዋሳ ሆቴል ተከናውኗል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሚልኪያስ ብትሬ ፣ የከተማው ባህል እና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ሀላፊ እና የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ደርጊቱ ጫሌ ፣ የከተማው የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ሀሚሶን ጨምሮ ስራ አስኪያጁ አቶ ኡቴሳ ኡጋሞ እና የክለቡ የቦርድ አባል ባዩ በልጉዳ እንዲሁም አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡
የክለቡ ስራ አስኪያጅ ባደረጉት ንግግር መርሐ-ግብሩ ከተጀመረ በኋላ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዳርጊቱ ደግሞ አስከትለው አጭር ንግግር አድርገዋል፡፡የከተማው ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት ሚልኪያስ ብትሬ በበኩላቸው “በእናንተ ድል ኩራት ይሰማናል። የሚያኮራ ውጤትም ነው ያስመዘገባችሁት። ከዚህም የበለጠ ውጤት ማምጣት ትችላላችሁ። በሦስተኝነት አንደኛውን ዙር አጠናቃችዋል። በቀጣይ ግን በሦስተኛነት ሳይሆን በአንደኝነት ማጠናቀቅ አለባችሁ። እኛም በማያሰለስ መልኩ ድጋፍ እናደርግላችዋለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ ለተጫዋቾች እና ለቡድኑ አጠቃላይ አባላት ከአራት መቶ ሺህ ብር በላይ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እና የዕራት ግብዣ ተከናውኖ ስነ ስርአቱ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡