ጋና ኢትዮጵያን በመጣል ለ6ኛ ተከታታይ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫው አቅንታለች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኮስታሪካው የ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከመጨረሻው የተጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና በድምር ውጤት 5-1 ተሽንፎ ከጉዞው ተገትቷል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአበበ ቢቂላው ሽንፈት ቤተልሔም በቀለ እና አርያት ኦዶንግን በማሳረፍ ነፃነት ፀጋዬ እና ማዕድን ሳህሉን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቶ ጨዋታውን ጀምሯል።

ጋናዎች ጨዋታ ከመጀመሩ ነበር ግብ ያስቆጠሩት። 2ኛው ደቂቃ ላይ በሁለቱም ጨዋታ ለኢትዮጵያ ፈተና የሆነችው አጥቂ አብዱላሂ ሳላማቱ በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ በተጣለላት ኳስ ፍጥነቷን ተጠቅም በመግባት ጋናን ቀዳሚ አድርጋለች። ከግቡ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቢመለስም ወደ ጋና ሳጥን ከመቅረብ የዘለለ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ቆይቷል። ይልቁኑም ጋናዎች በአዙማ በግሬ አማካይነት አስፈሪ ባይሆኑም ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ሁለት ሙከራዎችን አስመዝግበዋል።

የኢትዮጵያ ቀዳሚ ሙከራ 20ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ የማዕድን ሳህሉ የሳጥን ውጪ ጥረት በቀላሉ በጋናዋ ግብ ጠባቂ ፉንዲብ ኮላን ተይዞባታል። ሆኖም ኢትዮጵያዊያኑ ተጨማሪ ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት ሰላማቱ አብዱላሂ 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲሲሊያ ኒያማ የሰነጠቀችላትን ኳስ እንደመጀመሪያው ሁሉ አምልጣ በመግባት ከመረብ አገናኝታ ውጤቱን አስፍታለች።

በቅብብል ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ቢሞክሩም ከመሀል ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ያደርሱ የነበሩት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች የተሻለ የማጥቃት ጫናን መፍጠር በጀመሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች በጋና ሳጥን ዙሪያ የቅጣት ምት ዕድሎችን አግኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ 39ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከግራ መስመር ያሻማችውን የቅጣት ምት ኳስ መሳይ ተመስገን በግንባር በመግጨት ውጤቱን 2-1 አድርገዋለች።
በአጋማሹ ከታዩ ሌሎች ትኩሩት ሳቢ ሁነቶች ውስጥ 36ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት ፀጋዬ እና ዶሪስ ቦአድዋ ከባድ ግጭት አስተናግደው ነፃነት ወዲያውኑ በቤተልሔም የተተካችበት ዶሪስም ከፈቂቃዎች በኋላ ለመቀየር የተገደደችበት አንዱ ነበር። በሌላው አጋጣሚ ደግሞ 40ኛው ደቂቃ ላይ ማዕድን በድንቅ ሁኔታ የጋና ተጫዋቾችን አታላ ባደረሰቻት ኳስ ቱሪስት ለማ ግብ ብታስቆጥርም በመስመር ዳኛዋ የተሳሳተ ውሳኔ ተሽሮባታል።

ኝቦኝ የን በጋና ሳጥን መግቢያ ላይ ካቋረጠችው ኳስ ቱሪስት ሙከራ አድርጋ ወደ ላይ በተነሳባት አጋጣሚ ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመረው የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርሬል ቡድን ሌሎች ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግሯል። የተሻለ ብልጫ ወስደው አልፎ አልፎ ከመስመር ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ግብ ይልኩ የነበሩት ጋናዎችም ሙከራዎቻቸው ከሳጥን ውጪ የሚደረጉ እና እምብዛም አደገኛ ያልነበሩ ሆነው ታይተዋል። በኢትዮጵያ በኩል ቀጣዩ ሙከራ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ተቀይራ ገብታ የነበረችው እፀገነት ግርማ አረጋሽ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የላከችው እና ቱሪስት የጨረፈችላትን ኳስ ተቆጣጥራ ከቀኝ የጋና ጎል ከጠባብ አንግል ያደረገችው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

80ኛው ላይ ሰርዋ አፖንሻ እንዲሁም 85ኛው ላይ እፀገነት ከሳጥን ውጪ ኢላማቸውን የጠበቁ ከባድ ሙከራዎችን አድርገዋል። በ87ኛው ደቂቃ የጋናዋ ግብ ጠባቂ ፉንዲብ ኮላን የንግስት በቀለን ሙከራ ለማዳን ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቷ በቀይ ካርድ በዕንባ ታጅባ ከሜዳ የወጣችበት አጋጣሚ ሌላው ትኩረት ሳቢ ቅፅበት ነበር። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም ሌላ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በጋና 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የኢትዮጵያ የ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞም በጋና የ5-1 ሽንፈት ተደምድሟል። በዚህም ጋናዎች ለተከታታይ ስድስተኛ ጊዜ በ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኮስታሪካ ማቅናታቸው እርግጥ ሆኗል።

ያጋሩ