የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ የ17ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ የ17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ሀምበርቾ ዱራሜ ሦስተኛነቱን ሲያረጋግጥ አቃቂ ቃሊቲም አሸንፏል።

ሀምበሪቾ ዱራሜ ያለ መሸነፍ ጉዞውን አስቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል

08፡00 ሲል በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ለማጠናቀቅ ለሀምበሪቾ ዱራሜ ላለመውረድ ደግሞ ለሶዶ ከተማ ወሳኝነቱ ላቅ ያለው ጨዋታ ተከናውኗል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ ለማጥቃት ፍላጎት እንዳላቸው ያሳዩበትን የሜዳ ላይ እንቅሴቃሴ አስተውለናል፡፡ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ማጥቃት ወረዳው በመጣል ግብ ለማግኘት ሶዶ ከተማዎች የጣሩ ሲሆን በአንፃሩ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በበኩላቸው ከወትሮው ጨዋታቸው ዛሬ ተቀዛቅዘው ቢታዩም ኳስን ተቆጣጥሮ ከመጫወት ግን አልቦዘኑም፡፡

በዚህኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎችን በሁለቱ ቡድኖች በኩል ተመልክተናል፡፡ 5ኛው ደቂቃ ላይ የሶዶው ማንዴላ መለሰ ለማሻማት በሚል ወደ ግብ ያሻገራት ኳስ የላይኛው የግቡ አግዳሚ ብረት በግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ተጨማሪ እገዛ መትታ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡20ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሀምበሪቾ በኩል ምንያምር ጴጥሮስ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው አቡሽ አበበ ከግቡ ቋሚ ብረት እና በተጨማሪም በተከላካዩች ዕርዳታ አድኖበታል፡፡ ከእነዚህ ሌላ ብዙም የጠሩ ዕድሎችን መመልከት ባልቻልንበት ቀዳሚው አርባ አምስት ላይ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀር ልዑልሰገድ አስፋው ከመስመር አሸምቶ ታዬ ወርቁ ለጥቂት ያመለጠው ዕድል ሌላኛው የጨዋታው ሙከራ ነበር፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በመጠኑም ቢሆን ሶዶ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በተለይ በመስመር አጨዋወታቸው ታግዘው ከርቀት የሚመቷቸው ኳሶች ለግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ፈታኝ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ 56ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ገብሬ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ሲያሻማ ዘላለም እያሱ ከተቆጣጠራት በኋላ በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ በተከላካዮች ስትመለስ ጥበቡ ከበደ ከርቀት መትቶ በአስደናቂ ሁኔታ አስራት ሚሻሞ አውጥቶበታል፡፡

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ጥበቡ ከርቀት መትቶ አስራት ሲመልስ ከግቡ ትይዩ የነበረው በረከት ገብሬ ለማግባት ጥረት ሲያደርግ ከአስራት ሚሻሞ ጋር በመጋጨቱ ግብ ጠባቂው ላይ ጠንከር ያለ ጉዳት ደርሶ ለህክምና ጨዋታው ለሰባት ደቂቃዎች ተቋርጧል ፤ ግብ ጠባቂውም ለተጨማሪ ህክምና በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርቷል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ቡድኖች ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠር 0-0 ተደምድሟል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ ጅማ አባ ቡናን አሸንፏል

ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ ጠንከር ያለው በዝናብ የታጀበ ጨዋታ የአቃቂ ቃሊቲን የኳስ ቁጥጥር ብልጫን የጅማ አባ ቡናን ወጥነት የሌለው ረጃጅም ኳስ አስመልክቶናል፡፡ በዚህ በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ከርቀት ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ ብዙም ይህ ነው ሊባሉ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አላስተዋልንም፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ አቃቂዎች እንደነበራቸው ብልጫ ግብ ማስቆጠር ባይችሉም ከዕረፍት መልስ ግን 51ኛው ደቂቃ ላይ ካሊድ ሀሰን ከድር አድማሱ ላይ ሳጥን ውስጥ በሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጉልላት ተሾመ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ የጅማ አባ ቡና በሊጉ የመቆየት ዕድል ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።