በዚህ ረገድ አዎንታዊ መሻሻሎችን ብንመለከትም በቁጥር ረገድ በሊጉ እምርታን ካሳዩት ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ተስፋቸውን ወደ እውነታ በመቀየር በክለቦቻቸውም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጠቃሚ ተጫዋቾች ለመሆን ሲበቁ ፤ በቁጥር የሚልቁት ባለተሰጥኦ የሆኑ እና “ነገ የት ይደርሳሉ?” የተባሉ ተጫዋቾች ግን አማካይ አልያም ከዚያ ያነሰ ደረጃ ያላቸው ተጫዋቾች ሲሆኑ እየተመለከትን እንገኛለን።
በእግርኳስ የተጫዋቾች የዕድገት ፒራሚድ ላይ በተለይ በታችኛው የዕድሜ እርከን በርከት ያሉ ተጫዋቾች እንደመኖራቸው የፒራሚዱ ግርጌ ሰፊ ሆኖ በተቃራኒው ወደ ሙሉ ሰዓት እግርኳስ ተጫዋችነት በሚደረገው ጉዞ የተጫዋቾች ቁጥር እያነሰ በጠባቡ የፒራሚድ አናት ላይ እጅግ ውስን ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች እንደሚደርሱ ይታመናል። እንደዚሁ ሁሉ ሁሉም ከዕድሜ እርከን ቡድኖች ወደ ዋናው ቡድን የሚመጡ ተጫዋቾች በሙሉ በከፍተኛ የብቃት ደረጃ ማገልገል ወደሚችሉ ከዋክብት ይቀየራሉ ተብሎ ባይታመንም በሀገራችን አውድ ያለው የዕድገት ሂደት ግን ብዙ የሚያነጋግር ነው። አሁን ባለው የእግርኳሳችን ነባራዊ ሁኔታ ከዕድሜ እርከን ቡድኖች አድገው በሊጉ ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾችን በሦስት ከፍሎ መመልከት ይገባል።
የመጀመሪያው ጎራ በፍጥነት የጎመሩ ተጫዋቾች እና ቀስ በቀስ ጎልብተው በተሻለ ብቃት ክለቦቻቸውን ከማገልገል ባለፈ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ቁልፍ ሚናን በመወጣት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች የተካተቱበት ነው። በዚህ ውስጥ እንደነ አቡበከር ናስር ፣ ሱሌይማድ ሀሚድ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ሱራፌል ዳኛቸው ያሉ ተጫዋቾችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ሁለተኛው ጎራ ደግሞ ብዙ ተጠብቆባቸው ነገር ግን በታሰበው ልክ ወደፊት ሳይሄዱ የተየቀዛቀዙ ተጫዋቾች ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች ከዕድሜ እርከን ወደ ዋናው ቡድን ሲመጡ ተስፋ ሰጪ ብቃትን ቢያስመለከቱንም በሂደት ግን በጣም የተቀዛቀዘ የእግርኳስ ህይወት እያሳለፉ ይገኛሉ። አቡበከር ሳኒ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ አብዛኞቹ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ለዚህ ማሳያ ናቸው።
የመጨረሻው ጎራ የሚሆነው ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም አሁን ላይ ብቃታቸው ተዳክሞ ለመረሳት የተቃረቡ ተጫዋቾች ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች አጀማመራቸው ተስፋ ሰጪ የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን የሜዳ ላይ ብቃታቸው ከመዳከም አልፎ አሁን ላይ በእግርኳሱ ያላቸው ተፅዕኖ በጣም የቀነሰ ተጫዋች የሚገኙበት ስብስብ ሲሆን ለአብነትም ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ያሬድ ብርሃኑ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን መጥቀስ ይቻላል።
በዚህኛው ፅሁፋችን በመሰረታዊነት በሀገራችን ከፍተኛ የሊግ ዕርከን በሆነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያለውን ወቅታዊ የወጣት ተጫዋቾች ሁኔታ ላይ የምናተኩር ሲሆን በዋነኝነትም በሊጉ ወጣት ተጫዋቾች ሲጀምሩ ለምን ጥሩ ብቃት ያሳያሉ የሚለውን ጨምሮ በሂደት ግን ብቃታቸው መሻሻል ቀርቶ ይበልጥ እየተቀዛቀዙ ስለመሄዳቸው እና ይህን ሂደት ለመቀልበስ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ሀሳቦችን ልናነሳ ወደናል። በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን በተለይ በሀዋሳ እና አካባቢው በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ከመሰረታቸው በማሰልጠንም ሆነ በተለያዩ የሊጉ ክለቦች በተለያዩ ኃላፊነቶች መስራት የቻለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና በአሁኑ ወቅት በወልቂጤ ከተማ በዋና አሰልጣኝነት በመስራት ላይ የሚገኘው ተመስገን ዳና እና በአስኮ ፕሮጀክት በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ማፍራት የቻለው አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በቅድሚያ ለማንሳት የወደድነው ሀሳብ ወጣት ተጫዋቾች በሊጉ በአሁኑ ወቅት ስላላቸው አበርክቶ ነበር። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያነሳንላቸው ሁለቱ ባለሙያዎች በገዳዩ ላይ የተለያየ ምልከታ ያላቸው ሲሆን አሰልጣኝ ተመስገን በሊጉ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን እየተመለከትን እንገኛለን ሲል በተቃራኒው አሰልጣኝ ደስታ ግን የተለየ ሀሳብ አለው።
ተመስገን እንዲህ ይላል “ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን እየመለከትን እንገኛለን። ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ነው። ፌደሬሽኑ በዮዝ ዴቨሎፕመንት ዲፓርትመንቱ በኩል የሚያከናውናቸው የኢትዮጵያ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ውድድሮች ለወጣቶች ሰፊ ዕድል ፈጥረዋል ብዬ አስባለሁ። ሌላኛው ክለቦች ከዚህ ቀደም ይከተሉት ከነበረው አሰራር በተለየ አዲስ ፖሊሲ ማፅደቃቸው ነው። በዚህም ፖሊሲ በየዓመቱ አምስት እና ስድስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ማሳደጋቸው በርካታ ወጣቶች በሊጉ ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል። በተጨማሪም ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱ ከዚህ ቀደም ዕምቅ አቅም ያላቸው ወጣት ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ የነበረው የተጫዋቾቻችን ህልም በባህር ማዶ እስከ መጫወት ድረስ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይሁንና በታሰበው ደረጃ በትልቅ ደረጃ ለመጫወት የሚችሉ ተስፋ ያላቸው ተጫዋቾችን እንደመመልከታችን ያህል ከስር መሰረታቸው የሚገባቸው መሰረታዊ ሥልጠና ማግኘት ያልቻሉ ታች መጨረስ የሚገባቸውን ነገሮችን ያልጨረሱ ተጫዋቾችን እየተመለከትን እንገኛለን።”ሲል በተቃራኒው አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ደግሞ “በፕሪሚየር ሊጉ ለወጣት ተጫዋቾች በቂ ዕድል እየተሰጠ አይደለም። ዕድሉን ያገኙትም በበቂ ሁኔታ ብቃታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ የሚል ዕምነት የለኝም።” ሲል ሀሳቡን ይገልፃል።
ወጣት ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ በሚፈለገው ልክ እያየን ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ቢያከራክርም መሻሻሎችን ግን እየተመለከትን የመገኘታችን ነገር አያጠያይቅም። ነገርግን ሁሉንም የሚያስማማው ጉዳይ ግን አብዛኞቹ ወጣት ተጫዋቾች አጀማመራቸው ላይ ከፍ ብለው የመጀመራቸው ጉዳይ ግን የተለመደ ሂደት ነው ፤ ከዕድሜ እርከን ቡድኖች በተለያየ አጋጣሚዎች እና በተለያዩ አሰልጣኞች ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድልን ያገኙ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን መጥተው በሚያደርጓቸው የመጀመሪያ ወራት ጨዋታዎች ላይ ከዕድሜያቸው አንፃር በጣም የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በስፋት እናስተውላለን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በምክንያትነት የሚቀርበው ጉዳይ ወጣቶች ከታችኛው ቡድን ወደ ዋናው ሲያድጉ ራሳቸው በትልቅ ደረጃ ለማሳየት ያላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለ ሆኖ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ግን የስፖርት ቤተሰቡ ለወጣት ተጫዋቾች ያለው ጥሩ የሚባል አቀባበልም ሚና እንዳለው ያነሳል።
“ባለፉት ስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት በሊጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች እየተመለከትን እንገኛለን። ነገርግን እነዚህ ተጫዋቾች ከውጭ የመጡ ስለሆኑ ብቻ የተለየ ቦታ ቢሰጣቸውም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ግን በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑ እና ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች የተሻለ ነገር ለማየት አለመቻላችን በራሱ የስፖርት ቤተሰቡ ወጣት ተጫዋቾች ይህን ኃላፊነት ተረክበው እንዲጫወቱ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲኖረው አስገድዷል። ታድያ በዚህ ሂደት ወጣት ተጫዋቾች ብቅ በማለት ይህን አሰልቺ ሂደት የመከሰት ዕድሉን ማጥበብ በመቻላቸው በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ያለው አቀባበል እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል መሆኑ ሌላኛው ምክንያት ነው። ለማሳያነት አንድ ክለብ አንድ ወጣት ተጫዋች ወደ ሊጉ ሲያስተዋውቅ ደጋፊዎች በሚደግፉት ክለብ ሳይወሰኑ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው ይስተዋላል። ይህም እንደ ሀገር ወጣት ተጫዋቾችን የማየት ፍላጎት ስለመኖሩ ማሳያ ነው።”ይላል።
ሌላው ጉዳይ ግን እነዚሁ ወጣት ተጫዋቾች የፕሪሚየር ሊግ ህይወትን ከፍ ባለ የብቃት ደረጃ መጀመር ቢችሉም በሂደት ግን ብቃታቸው ጠብቀው ከተቻለም ራሳቸው ማሻሻል ቀርቶ ይበልጥ የነበራቸውንም ነገር እያጡ በሂደት እየተቀዛቀዙ የመሄዳቸው ጉዳይ አሳሳቢው ጉዳይ ነው። ለዚህም በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ይቀርባሉ።
ሁለቱም ባለሙያዎች በተለይ የተጫዋቾች የግል ስብዕና እና በክለቦች ውስጥ ያለው የሥልጠና መንገድ ላይ በአፅንኦት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ተመስገን በጉዳዩ ዙርያ ይህን ብሏል
“ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው በመሰረታዊነት እንደየተጫዋቹ የግል ስብዕና የሚለያይ ነው። ሌላው የክለቦች የስልጠና መንገድ በራሱ ተፅዕኖ አለው በተጨማሪም የሚሰጣቸው ኃላፊነት ክብደት እና ቅለት ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ነው። እንዲሁም ተጫዋቾች በዕድሜ ዕርከን ቡድኖች በነበሩበት ወቅት የነበራቸው የእግርኳስ ግንዛቤ በራሱ ልዩነት ይፈጥራል። የእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ድምር ውጤት ወጣት ተጫዋቾች ይዘው የመጡትን አቅም አሳድገው እንዳይቀጥሉ አድርጓል ብዬ አምናለሁ።” ይላል።
አሰልጣኝ ተመስገን ጉዳዮቹን በዝርዝር ሲያብራራም “የግል ስብዕና ስንል ተጫዋቾች እንደመጡ በብዙ ነገሮች ጥሩ ሆነው ትመለከታለህ። በጣም ዲሲፕሊንድ ሆነው የሚሰጣቸውን ለመቀበል የተሰጣቸውን ሜዳ ላይ ለመተግበር ከፍተኛ ፍላጎት ትመለከትባቸዋለህ። ነገር ግን በሂደት ምናልባት ሁኔታዎቹ በራሱ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ከዛ ውጪ የራሳቸው ስብዕና ሲጎዳቸው እንመለከታለን። በትንሽ ነገር (አድናቆት ፣ ገንዘብ ፣ ስም) የመርካት እና በቂ ነው ብሎ አምኖ የመቆም ፣ በአቻ ግፊት ከመስመር የመውጣት ፣ ሥልጠናዎችን በተገቢ ሁኔታ አለመከታተል ፣ የቀደመ ተሳትፏቸው በብዙ መልኩ መቀነስ ፣ በይበልጥ ወደ መዝናናት ማድላትን እንመለከታለን እንዲሁም የመስራት ፍላጎታቸውም ተቀዛቅዞ ይታያል። ከዚህ ቀደም ከቡድን አጋሮቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነትም ከቀደመው አንፃር ወርዶ ትመለከታለህ።” ከሚለው አሰልጣኝ ተመስገን ሀሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ አሰልጣኝ ደስታም አጋርቶናል።
“ከታች ይዘውት የመጡት ተነሳሽነታቸው በሂደት ከጨዋታ ጨዋታ እየቀነሰ ይሄዳል። ከዚያ ባሻገር ከገንዘብ ጋርም ሊያያዝ ይችላል። የእኛ ተጫዋቾች ጥሩ የህይወት ክህሎት (Life Skill) ተምረው ስለማይመጡ ገንዘብ ሲመጣ ህይወታቸውን በሚጎዳ መልኩ የመጠቀም ነገር ሊኖር ይችላል። ይህም አንዱ ምክንያት ነው።”
በክለቦች ስላለው ደካማ ሥልጠና ጋር ስለተያያዘው ጉዳይም አሰልጣኝ ደስታ ተከታዩን ብሏል
” በሀገራችን ክለቦች ወጣት ተጫዋቾች ያላቸውን ብቃት ጠብቀው ለመሄድ የሚያስችል ሥልጠና አለ የሚል ዕምነት የለኝም። በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ ከታች ከታዳጊዎች እስከ ላይ ድረስ ያለው ሥልጠና አሰጣጣችን በጣም ደካማ ነው። ከቴክኒክ ፣ ከታክቲክ ፣ ከአካል ብቃት እና ሥነልቦና ጋር ተያይዞ እየተሰጡ የሚገኙ ሥልጠናዎች ተጫዋቾችን የሚያበቁ አይደሉም። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በዋናው ቡድኖች ደረጃ ያለውን ሂደት ለመመልከት ጥረት ሳደርግ በተለይ በዋና ቡድን ደረጃ የሚጠበቀው የታክቲክ ሥልጠና እግርኳስ አሁን ከደረሰበት ነገር አንፃር በቂ ነው የሚል ዕምነት የለኝም። ታዳጊ ተጫዋቾች ከታችም በቂ ሥልጠና ሳያገኙ ይመጣሉ ዋናው ቡድንም ከደረሱ በኋላ በተለይ ከታክቲክ ሥልጠና ጋር በተያያዘ በቂ ልምድ አያገኙም የሚል ነገር ነው ያለኝ። በጥቅሉ እነዚህ ጉዳዮች አሁን ድረስ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የምንመለከታቸው ችግሮች በስተጀርባ ያሉ ናቸው። በተለይ በታክቲኩ ያለውን አነሳን እንጂ በሌሎቹም በኩል ያለው ነገር ተመሳሳይ ነው ይህ ደግሞ ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ብቃታቸውን ጠብቀው እንዳይጫወቱ የሚያደርግ በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ነው።” ሲል ያነሳል።
ከታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና አንስቶ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በተለያየ ኃላፊነት ማሰልጠን የቻለው ተመስገን ዳና በሥልጠና ዙርያ ይህን ይላል ፤
“የክለቦች የሥልጠና መንገድ በራሱ የወጣቶቹን ዕድገት ይገድበዋል። ወጣቶች ከታች ሲመጡ ያላቸውን ጠንካራ እና ደካማ ነገር በመረዳት ‘በደካማዎቹ ላይ እንዴት መሻሻል ይችላል ? እንዲሁም ጠንካራ ጎናቸውን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል ?’ በሚለው ዙርያ ሥልጠናዎች አይሰጧቸውም። ምክንያቱም በፕሪሚየር ሊጉ የሚገኙ ክለቦች አብዛኞቹ ውጤት ተኮር በመሆናቸው የወጣቶች ግለሰባዊ ዕድገት ላይ ትኩረት አይሰጡም። ይህ ነገር ወጣቶቹ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። በተመሳሳይ ወጣቶቹ የሜዳ ላይ ብቃታቸው ትንሽ ወረድ ሲል ክለቦቹ ትዕግሥት አይኖራቸውም። ምክንያቱ የሚያያዘው ከውጤት ጋር ስለሆነ ነው።
ከላይ ከተነሱት ሀሳቦች በተጨማሪም ተመስገን ዳና እነዚህም ጉዳዮች ተፅዕኖ ያሳድራሉ ሲል ይናገራል።
“ከሚሰጣቸው ኃላፊነት አንፃር ከተመለከትነው ወጣቶች ወደ ሊጉ ሲመጡ ከትልልቅ ሲኒየር ተጫዋቾች በበለጠ የቡድኑ ብቸኛ ውጤታማነት መሰረት ተደርገው ይታያሉ። ያ ሳይገኝ ሲቀር ደግሞ ተጫዋቾችን ከመስመር የማውጣት ነገር እንመለከታለን። ሌላኛው ትልቁ ችግር ብዬ የማስበው ወጣቶች በዕድሜ እርከን ቡድኖች በሚኖራቸው ቆይታ በቂ ሥልጠና እና የእግርኳስ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አለመደረጉ በራሱ ላይኛው ሊግ ላይ ሲመጡ ትልቁ ፈተና ነው።”
በተሻለ የብቃት ደረጃ ጀምረው በሂደት የመቀዛቀዛቸው ነገር በሊጉ የተለመደ አዝማሚያ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ እግርኳሳችን በፍጥነት ምላሽ ሊያበጅለት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው። ይህ መሆን የማይችል ከሆነ ግን በእግርኳሳችን በሚኖረው የትውልዶች መተካካት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን ይችላል። ታድያ እኛም በመጨረሻም ይህ እንዳይሆን መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሁለቱ ባለሙያዎች የመፍትሔ ሀሳቦቻቸውን እንዲያጋሩን ጠይቀናቸዋል።
“መሰረታዊው የመፍትሔ ሀሳብ የሚሆነው ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ከማደጋቸው በፊት ሁለንተናዊ የሆነ ዕድገታቸው ላይ በደንብ መስራት ይኖርብናል። አንድ ወጣት ተጫዋች ወደ ዋናው የሀገሪቱ ከፍተኛ የውድድር ዕርከን ከመምጣቱ በፊት ምን ምን ማሟላት አለበት ? ከዚህ በፊት የነበሩት ተጫዋቾች ምን ምን ማሟላት ባለመቻላቸው ነው የጠፉት ?’ የሚለው ነገር ጥልቅ ጥናት በማድረግ ወደ መፍትሔው መምጣት ይገባል ብዬ አስባለሁ።”
“በሥልጠና መንገድ ፣ ተጫዋቾችን ቀርቦ በማነጋገር እና ተደጋጋሚ ዕድሎችን በመስጠት ሊቀረፍ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በቴክኒክ ክህሎቱ የላቀ በታክቲክ ግንዛቤው የበለፀገ በአዕምሮ ጠንካራ የሆነ ስኬትንም ውድቀትንም በቀላሉ መቋቋም የሚችል ፣ ከአቻ ግፊት ራሱን ለማራቅ የሚችል ፣ በአስተሳሰቡ ጠንካራ የሆነ ፣ ለግሉም ሆነ ለሀገሩ ጠንካራ ህልም ያለው ወጣት እንዲፈራ መስራት የግድ ይለናል። የተሟሉ ወጣት ተጫዋቾች ማሳደግ ከቻልን ላይኛው ሊግ ላይ አይቸገሩም። በምንም ዓይነት ጫና ውስጥ እንኳን ሆነው በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ልጆችን ማፍራት እንችላለን። በቂ ሥልጠና ባላገኙበት ሁኔታ ማደግ ስላለበት ብቻ የምናሳድግ ከሆነ የተጫዋቹን ዕድገት ያቀጭጨዋል ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም በላይኛው ዕርከን ላይ ይህን ለመስራት አመቺ ስላልሆነ ይበልጥ በታችኞቹ ዕርከኖች ላይ ጠንካራ ሥራዎችን መስራት ይኖርብናል።” የተመስገን ዳና ሀሳብ ሲሆን አሰልጣኝ ደስታ ደግሞ ይህን ይላል ፤
“በእኔ ዕምነት ይህ እንዳይሆን መሰረታዊው በዋናው ቡድን ደረጃ የሚገኙ አሰልጣኞች ሥራ መሆን ያለበት ወጣት ተጫዋቾችን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ መሆን ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ልጆቹን የሚረዱ በቂ የሆኑ ስልጠናዎችን መስጠት የግድ ይላል። ሌላው ከህይወት ክህሎት እና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁ ጥረቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እንደሚታወቀው በሀገራችን በቂ የሆኑ የስፖርት የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሉም። ነገር ግን አሰልጣኞች ራሳቸው በማማከር እና በመምከር ወጣት ተጫዋቾች ብቃታቸውን ጠብቀው የተሻለ ተጫዋች እንዲሆኑ የሥነልቦና ድጋፍ እንዲሁ እንዲያገኙ መደረግ ይገባል።”
ከጊዜ ወደ ጊዜ በዋናው ቡድን የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ተጫዋቾቹ በሚፈለገው መጠን ራሳቸውን አጎልብተው የላቁ ተጫዋቾች መሆን ካልቻሉ በአጠቃላይ ሂደቱን ረብ የለሽ የሚያደርጉት መሆኑ ግልፅ ነው። በመሆኑም ታዳጊ ተጫዋቾች በተለይ ከ6 ወይንም ከ8 ዕድሜያቸው መነሻነት በዕድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ሥልጠና እየሰጠን ወደ ላይ ማብቃት ካልተቻለ አሁን እንደያዝነው ዓይነት በበቂ ሥልጠና ያልመጡ ወጣት ተጫዋቾችን ከረፈደ መሰረታዊ ሥልጠናዎችን የመስጠት አዝማሚያ ከብዙ መመዘኛዎች አንፃር ውጤታማነቱ አጠያያቂ ነው።
ተጫዋቾቹ ወደ ዋናው ቡድን ከደረሱ በኋላም በክለቦች ያለው ኋላ ቀር የሆነ ስለዛሬ ብቻ የማሰብ ዝንባሌ እስካልተቀረፈ ድረስ ለወጣት ተጫዋቾች አመቺ የሆነ የዕድገት ከባቢን መፍጠር በጣም ከባድ እንደሆነ እየታዘብን እንገኛለን። በመሆኑም ነገን ዛሬ ላይ ስለመገንባት የሚያስቡ የእግርኳስ አመራሮች እና ክለቦችን መፍጠር ካልቻልን ወጣቶቻችን ማባከናችን አይቀሬ ነው።