ቤትኪንግ ለክለቦች በሚያሰራቸው መለያዎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ክለቦች በራሳቸው የሚፈፅሟቸው የመለያ ስምምነቶች እና ቤትኪንግ የሚያሰራላቸው መለያዎች የፈጠሩት ውዥምብርን የተመለከተ ምላሽ በመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ተሰጥቷል።

ዛሬ ከቀትር በኋላ በሳፋየር አዲስ ሆቴል በነበረ ሥነ ስርዓት ኢትዮጵያ ቡና ነገ በሚጀምረው በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች አንስቶ የሚጠቀምባቸውን መለያዎች ከአጋሩ ከ ‘ሀ እስከ ፐ’ ተረክቧል። በሥነስርዓቱ ላይ ከተሰጠው መግለጫ በኋላ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የሊጉን የስያሜ መብት የያዘው ቤትኪንግ ለተሳታፊ ክለቦች ‘መለያ አሰራለሁ’ ስለማለቱ ተነስቷል። ተቋሙ ይህንን ቢልም ክለቦች ከሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ድርጅት ጎፈሬ ጋር እንዲሁም እንደዛሬው እንደ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከአጋር ተቋሞች ጋር የመለያ አቅርቦት ስምምነት እየፈፀሙ መሆናቸው መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።


በዛሬው መድረክ በጉዳዩ ላይ የተነሳው ጥያቄም የነገሩ ግልፅ አለመሆን ክለቦች ከሁለት ተቋማት ጋር እርስ በእርስ የሚጣረስ ስምምነት እየፈፀሙ እንዳሉ የሚያስመስል በመሆኑ ማብራሪያ እንዲሰጥበት የሚል መነሻ ነበረው። በዚህም ክለባቸውን ወክለው ቢገኙም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጉዳዩን የሚያጠራ ምላሽ ሰጥተውበታል።

የቦርድ ሰብሳቢው በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ቤትኪንግ ‘እንደ ማበረያቻ መለያችሁን አሰራለሁ’ በማለት እንደነበር ቃል የገባው በማንሳት ማብራሪያቸውን ጀምረዋል። ክለቦች ይህንን በፍቃደኝነት የተቀበሉ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይ ግን ተቋሙ ያነሳውን ጥያቄ እና የክለቦችን ምላሽ እንዲህ አስረድተዋል። “ቤትኪንግ የእኔን አራማ ጀርባ ላይ ወይንም ደረት ላይ አድርጉልኝ አለ። እንደገና ክለቦችን ጠየቅናቸው። ከተጠየቁት ክለቦች ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ‘በመጀመሪያ ከተደረገ የታይትል ስፖንሰርሺፕ ውጪ የቤትኪንግን አርማ ጀርባ ላይም ሆነ ደረት ላይ አናደርግም’ በሚል አንቀበልም አሉ።”

በዚህም መሰረት አርማውን በመለያቸው ላይ ለማድረግ የፈቀዱት ክለቦች በራሳቸው ቀለም መለያው ተሰርቶ መጥቶ በዚህ ሳምንት ርክክብ እየተደረገ እንደሆነ መቶ አለቃ ፍቃደ ገልፀዋል። በመጨረሻም “መለያው የጎፈሬን የሚተካ አይደለም ፤ በራሳቸው ከለር እነርሱ በፈቀዱት መንገድ የተሰራ ነው።” በማለት ለጥያቄው የሰጡትን ምላሽ አጠቃለዋል።