የኢትዮጵያ ቡና አጋር ድርጅት የሆነው ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ መጫወቻ መለያዎች እና ትጥቆችን ለክለቡ አስረክቧል።
ዛሬ ከ10:00 ጀምሮ በሳፋየር አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ ሥነ ስርዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከዚህ በኋላ የሚጠቀምባቸውን ሦስት ዓይነት መለያዎች አስተዋውቋል። ክለቡ በአጋሩ ‘ከሀ እስከ ፐ’ የቀረቡለት መለያዎች ይፋ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ ፕሬዘዳንት የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ሞሞ ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና የ ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ አመራር የሆኑት አቶ ፍሬዘር አብይ በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የዕለቱ ሥነ ስርዓት ሲጀምር ከ19970ዎቹ ጀምሮ ቡና በተለምዷዊነት የሚጠቀማቸው የቡና እና ቢጫ መለያዎች እና ሌሎች የተለዩ ቀለማት የነበራቸው መለያዎች ለዕይታ ቀርበዋል። በመቀጠል መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክለቡ ፕሬዘዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከሀበሻ ቢራ ጋር መስራት ከጀመሩ አንስቶ መለያ ሲያቀርብላቸው ከነበረው ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ ጋር አብሮ የመስራት ልምድ እንዳላቸው በመግለፅ ከተቋሙ ጋር በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ኪሎ በሚገኘው አምባሳደር ህንፃ ላይ የብራንድ ሱቁ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚከፍት ተናግረዋል።
በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት ሥራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ውልዴ ዝርዝር ጉዳዮችን አብራርተዋል። ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ቀደም ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ ጋር የብራንድ ሱቅ ለመክፈት በተገባው ውል ላይ ተቋሙ ደረጃቸውን የጠበቁ ትጥቆች ለክለቡ ለማቅረብ መስማማቱን አንስተው ለሁለቱም ፆታዎች ሁሉም የዕድሜ እርከን በድኖች የሚሆኑ 500 የመጫወቻ ሙሉ ትጥቆች ፣ ለዋናው ቡድን እና ለአሰልጣኞች 100 ቱታዎች እና 50 የአሰልጣኝ ስታፍ ቲሸርቶች ርክክብ እንደሚፈፅሙ ተናግረዋል። የእነዚህ ትጥቆች አጠቃላይ ዋጋ ሦስት ሚሊያን ሀያ አምስት ሺህ መሆኑንም አቶ ገዛኸኝ ገልፅው በመለያው እጅጌ ላይ የ ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ አርማ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
የ’ከ ሀ እስከ ፐ’ አመራር የሆኑት አቶ ፍሬዘር አብይ ደግሞ ከተለመዱት ቀለማት መለያዎች በተጨማሪ ሦስተኛ መለያ ማቅርባቸውን ተናግረው ብራንድ ሱቁ ወደ ማለቁ መድረሱን የውስጥ ዲዛይኑ አልቆ ዕቃዎች መግባት መጀመራቸውን አንስተዋል። በሱቁ የሚኖሩት ዕቃዎች 50 በመቶው ከሀገር ውስጥ 50 በመቶው ደግሞ ከውጪ እንደሚሆኑ ገልፀው ሱቁ ክለቡን በፋይናንስ የመደገፍ ዓላማ ያለው በመሆኑ ደጋፊው ምርቶቹን ከሱቆቹ ብቻ እንዲገዙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመቀጠል ለተነሱት ጥያቄዎች አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ምልሽ ሰጥተዋል።
‘ከ ሀ እስከ ፐ’ ከስምምነቱ ስለሚጠቀሙበት አግባብ
“በሬድዮ ፕሮግራማችን እና በመለያችን ላይ ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ን የማስተዋወቅ ስራዎች ይሰራሉ። በዋናነት ግን በመለያው እጅጌ ላይ የድርጅቱ አርማ እንዲታተም ተደርጓል። በሪፕሊካውም ላይ በተመሳሳይ የሚደረግ ነው።”
ተመሳስለው ስለሚሰሩ መለያዎች
“ይሄ በጣም የፈተነን እና ክለባችንን ለመጥቀም በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ችግር የፈጠረብን ያለ ተግባር ነው። በተየለያየ መንገድ ለመግለፅ ሞክረናል። ብዙ ደጋፊዎች እየተባበሩን ነገሮች እየቀነሱ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ቆሟል ማለት አይችልም። ከዚህ በኋላ ደፍሮ ወደ ሕግ መግባትን የሚጠይቅ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በአዕምሮ ንብረት ባለስልጣን የተመዘገበ ብራንድ ነው። ስለዚህ ከክለቡ ውጪ ማንም ሊጠቅምበት አይችልም። ከጠቀመበት በወንጀል ይጠየቅበታል። ያንን ነገር ገፍተን መስራት ላይ መሰረታዊ ችግር ያለብን ይመስለኛል።”
ከብራንድ ሱቁ ክለቡ ስለሚያገኘው ጥቅም
“አርማውን ለ’ከ ሀ እስከ ፐ’ በመስጠቱ ከሁሉም ሽያጭ ላይ 20℅ የሮያሊቲ ክፍያ ይቀበላል። ከትርፉ ደግሞ በየሦስር ወሩ ወይንም በተርም እንደገና ይካፈላል። ይህ የሚመራው ከክለቡ እና ከተቋሙ በተወጣጡ ሰዎች በተቋቋመ ኮሚቴ ይሆናል።”
ከዚህ ውጪ በመድረኩ ላይ ሪፐሊካ መለያዎች በተለያየ ዲዛይን እንደሚቀርቡ ፣ ብራንድ ሱቁ ውስጥ ከመለያዎች እና ትጥቆች ውጪ የተለያዩ ቀሳቁሶች የደጋፊዎችን አቅም ባገናዘበ የተለያየ የዋጋ አማራጭ እንደሚቀርቡ እና ሁሉንም ሰው የሚስተናገድበት እንደሚሆን ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ መጨረሻ ላይ ሦስቱ መለያዎች በተጨዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ተለብሰው ለዕይታ ቀርበዋል።