በሁለተኛው ዙር ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማሮ ዙርያ የተዘጋጀ ጥንቅር

የመጀመርያው ዙር በሁለት የተመረጡ ከተሞች ተካሂዶ ከተጠናቀቀ በሏላ ነገ በሚጀምረው የሁለተኛው የውድድር ዘመን አገማሽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዙርያ ተከታዩን ጥንቅር አሰናድተናል።

ሊጉ የውድድሩ አጋማሽ ከተጠናቀቀ በኃላ ከአንድ ወር በላይ እረፍት ተሰጥቶ በነገው ዕለት ሁለተኛው ዙር ሲጀምር ከ16ኛ እስከ 21ኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚካሄድ ይሆናል። ኮሮና ወረርሺኝን አስታኮ ዐምና በአዲስ የውድድር አቀራረብ ሊጉ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ከዚህ ቀደም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውድድሮችን ስትከውን የቆየችው አዳማ ለመጀመርያ ጊዜ አስተናጋጅ ከተማ ሆና ቀርባለች። የውድድሩ የበላይ አካል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አባላት ከቀናት በፊት አዳማ መግባታቸው ሲታወቅ የጨዋታ ታዛቢ (ኮሚሽነር) እና ዳኞችም አዳማ ከተማ ደርሰዋል። ከዳኞቹ መካከል በላይ ታደሰ ፣ ኃይለየሱስ ባዘዘው ፣ ለሚ ንጉሴ ፣ አሸብር ሰቦቃ እና ሊዲያ ታፈሰ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች ሲሆኑ ትግል ግዛው እና ሸዋንግዛው ተባበል ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ናቸው። በአጠቃላይ አስራ ሦስት ዋና እና ረዳት ዳኞች ከፌደራል ዳኞች መካከል ተካተዋል።

 

በአዳማ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ሆቴሎች በማረፍ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ የሰነባበቱ ክለቦች እንዳሉ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡና ለቡ በሚገኘው የክለቡ ካምፕ ቆይታውን እያደረገ የወድድሩ አንድ ቀን ሲቀረው በመምጣት ጨዋታውን በማድረግ እየተመላለሰ ውድድሩ እንደሚጨርስ ሲታወቅ ቅዱስ ጊዮርጊስም ቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ቆይታውን እንደሚያደርግ ሰምተናል። በተመሳሳይ መከላከያም በቢሸፍቱ ከተማ ማረፊያው እንደሆነ አውቀናል። ጨዋታቸውን በመጨረሻ ዕለት የሚያደርጉት ወላይታ ድቻዎች ምሽቱን አዳማ ሲደርሱ ድሬዳዋ ከተማዎች እስካሁን ያልገቡ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኮቪድ ምርመራ በዩኒቨርሲቲው ስታዲየም ዙርያ በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ ሲሆን የመልበሻ ክፍል፣ የጋዜጠኞች ስፍራ፣ የመፀዳጃ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን ታዝበናል። በጨዋታ ማስተላለፍ ፣ በአቅራቢነት እና ተንታኝነት ሰዒድ ኪያር ፣ መኳንንት በርኼ እና ዮናስ አዘዘ እንደሆኑ ሲታወቅ እንደየአስፈላጊነቱ የእግርኳስ ባለሙያዎች በተንታኝነት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በፀጥታ ዘርፍ ከከተማው የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁን እና ክለቦች ባረፉበት ሆቴል በልምምድ ሜዳዎች ጥበቃዎች ሲደረጉ ተመልክተናል። ነገ በሚኖረው የመክፈቻ ጨዋታ ላይም የተለየ የማድመቂያ ሥነ ስርዓት እንደሚኖር ሲጠበቅ የስታዲየም ፓውዛውን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ታዝበናል።

በከተማው ሦስት የልምምድ ሜዳዎች ተዘጋጅተዋል። አበበ ቢቂላ ስታዲየም፣ ወንጂ ሜዳ እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ግቢ የተዘጋጁ ሲሆን በተጨማሪነት አንድ ሜዳን በአማራጭነት ለመጠቀም መታሰቡን አውቀናል። የደጋፊዎች መግቢያ በር የዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደት እንዳያደናቅፍ የተለየ ዝግጅት ተደርጎ ለስታዲየሙ ቅርበት ባለው አቅጣጫ መዘጋጀቱ ተገልፆል። ከቀናት በፊት ይፋ በሆነው የመግቢያ ዋጋ መሰረትም 1ኛ ደረጃ 200 ብር፣ 2ኛ ደረጃ 100 ብር፣ 3ኛ ደረጃ 50 ብር፣ 4ኛ ደረጃ 20 ብር ሆኗል።

የኮቪድ ምርመራን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አንድ ተጫዋች በመጀመርያው ምርመራው ፖዘቲቭ ከተባለ ከጨዋታ ውጭ እንደሚሆን ሲታወቅ ከዚህ በኃላ በሚኖረው ምርመራ ግን የመጀመርያውን ፖዘቲቭ ቢባል ለሁለተኛ ምርመራ ዕድል እንደሚሰጥ አውቀናል።

የውሃ ዕረፍትን በተመለከተ የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ ብቻ ከዕረፍት በፊት 25ኛው ደቂቃ ከዕረፍት መልስ 75ኛው ደቂቃ ብቻ እንደሚኖር እና በምሽቱ ጨዋታ ወቅት የውሃ ዕረፍት እንደማይኖር ተረጋግጧል።

48 ጨዋታዎች የሚካሄዱበት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩነነቨርስቲ ሜዳ ነገ የመክፈቻ ጨዋታ ሲያደርግ ዘጠኝ ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ከሰበታ ከተማ እንዲሁም ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ፋሲል ከነማ ከሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።