ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ሲመለስ ቀዳሚውን ግጥሚያ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
የሁለተኛው ዙር መባቻ የሆነው ጨዋታ ነገ 09:00 ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ሲጀምር በሰንጠረዡ እናት እና ግርጌ ላይ የሚገኙ ክለቦችን ያገናኛል። እስካሁን ምንም ሽንፈት ያላስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዙሩን በድል መጀመር ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት ካሁኑ የማስፋት ዕድል የሚሰጠው በመሆኑ ትርጉሙ ቀላል የሚባል አይሆንም። ከአስር ነጥብ በታች ያለው ብቸኛው የሊጉ ክለብ ሰበታ ከተማ በበኩሉ በሊጉ የመቆየቱ ነገር ከጅምሩ ነጥቦችን በመሰብሰብ ካልታጀበ ችግር ውስጥ መግባቱ አይቀርም።
የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዙር ጉዞ የተዋጣለት ለመባል የቀረበ ነበር። በርካታ ጎል በማስቆጠር በፋሲል ከነማ ብቻ የተበለጠው ጊዮርጊስ መረቡም ስድስት ጊዜ ብቻ ነበር የተደፈረው። ወጥ የኋላ ተከላካዮች ጥምረት በመያዝ እና በኢስማኤል ጎር አጎሮ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ታጅቦ ስምስት ጨዋታዎችን በድል በመወጣት በሰባቱ ነጥብ ተጋርቶ ጨርሷል። በአጨዋወት ደረጃም ቡድኑ በአሰልጣኝ ዘሪሀን ሸንገታ ስር ቀድሞ ወደሚታወቅበት ቀጥተኝነት መመለሱ ይበልጥ ውጤታማ እና ለተጋጣሚዎች አስቸጋሪ አድርጎት ታይቷል። እርግጥ ነው ወደ ማብቂያው ላይ በሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ የተጠና መከላከል መቸገሩ በሁለተኛው ዙር ከፍ ያለ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ምልክት የሰጠ ነበር። የነገ ተጋጣሚው በዚህ ረገድ ያለበት ድክመት ግን ለጊዮርጊስ ብዙ ስጋት የሚሆን አይመስልም።
ወደ ሰበታ ከተማ ስንመጣ ቁጥሮች ከነገ ተጋጣሚው የተቃረኑ ሆነው እናገኛቸዋለን። አንድ ብቸኛ ድል ያስመዘገበው ሰበታ በሊጉ ብዙ ግብ ከማያስቆጥሩ ቡድኖች ጋር ያልተራራቀ የግብ መጠን ቢኖረውም በርካታ ግቦችን በማስተናገድ ግን ቀዳሚ ነው። በዚህም የደረጃውን ግርጌ ከጅማ አባ ጅፋር ለመረከብ ሲገደድ ከወራጅ ቀጠናው መግቢያ የሰባት ነጥቦች ርቀት ላይ ይገኛል። በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስር ዓመቱን የጀመረው ሰበታ ያልተረጋጋ ምርጥ 11 መገለጫው ነበር ማለት ይቻላል። ተለዋዋጭ የአሰላለፍ ምርጫው በመከላከልም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ይህ ነው የሚባል ጥንካሬ ሳያሳይ ነበር ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየው። በሌላ በኩል ሁለት ጨዋታ ሲቀር ኃላፊነቱን የተረከቡት አሰልጣኝ ብርሀኑ ደበሌ የመሯቸውን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት መጨረሻቸው ለቡድኑ የነገ ጨዋታ ጥሩ መነሻሻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አሁንም በደመወዝ ውዝግብ ምክንያት በተጫዋቾች መሀከል ያለው ጥያቄ አለመመለስ እና በዚሁ ሳቢያ ልምምድ ከጀመሩ ገና አንድ ሳምንት ብቻ መቆጠሩ ከመጋቢት 03 ጀምሮ በልምምድ ላይ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንፃር ለሰበታ ስጋት ነው።
በውድድሩ አጋማሽ በነበረው የዝውውር ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈጥሯዊ የግራ መስመር ተጫዋች ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ባደረገው ጥረት ያሬድ ሀሰንን ሲያስፈርም ሰበታ ከተማ ደግሞ ጋናዊው ቢስማርክ አፒያን የፊት መስመሩን ለማጠናከር ወደ ቡድኑ አምጥቷል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ከነዓን ማርክነህ ከጉዳት ሲመለስ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ አጥቂዎቹ እስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ቡልቻ ሹራ ግን በጉዳት ጨዋታው ያልፋቸዋል። በሰበታ ከተማ በኩል በጉዳትም ሆነ በቅጣት ከጨዋታ ውጪ የሚሆን ተጫዋች የለም፡፡
ጨዋታውን አሸብር ሰቦቃ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ትግል ግዛው እና ሻረው ጌታቸው በረዳትነት ባህሩ ተካ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።
የእርስ እርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ በአጠቃላይ በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በአራቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ 15 ጎሎች ሲቆጠሩ አስሩን ጊዮርጊስ አምስቱን ሰበታ አስቆጥረዋል።
– ሊጉ ከረጅም ከዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።