ቅደመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተነው አዘጋጅተናል።
በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው እና የታችኛው ፉክክር ላይ በነጥብ ቀርበው የሚገኙት ፋሲል እና ሀዲያ ሆሳዕና ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት ነጥብ ርቆ ያለው ፋሲል ከነማ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያሚያደርገውን ውጤት ለማግኘት ከነገው ጨዋታ መሉ ነጥብ ይፈልጋል። ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ብቻ ከፍ ያለው ሀዲያ ሆሳዕና ነጥቡን ሀያ ለማድረስ የፋሲልን ፈተና የሚጋፈጥ ሲሆን ከተሳካለት ግን ወደ ሰንጠተዡ ወገብ የመሳብ ዕድል ይኖረዋል።

የነገ ተጋጣሚው ላይ ያስመዘገበውን ጨምሮ ሦስት ተከታታይ ድሎችን በማሳካት ዓመቱን የጀመረው ፋሲል ቀጣይ ጉዞው እንዳሰበው አልሆነለትም። ከቻምፒዮንነት ማግስት የሚጠበቀውን ከባድ የውድድር ዘመን ባልተጠበቁ ጨዋታዎች ነጥብ በመጣል ጀምሮ አልፎ አልፎ ሰፋፊ ድሎችን በማስመዝገብ በአንፃሩ ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈቶች እየገጠሙት የመጀመሪያውን ዙር አገባዷል። እንዲያም ሆኖ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰው ፋሲል በቁጥር የተጋነነ ባይሆንም ከአምናው በስብስብ የተጠናከረው የኋላ ክፍሉ ያስተናገደው የግብ ብዛት የሚያሳማው ነበር። የውድድር አጋማሽ ዝውውር ያልፈፀሙት አፄዎቹ የቀድሞው አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም ግልጋሎትን በሁለተኛው ዙር የሚያገኙ መሆኑ ቡድኑ የግብ መጠኑን ይበልጥ እንዲያሻሽል በር ከፋች ሊሆንለት ይችላል። ነገር ግን ሜዳ ላይ አልፎ አልፎ የሚታይበት መቀዛቀዝ እና ከወገብ በታች ያለው መዋቅሩ የሚላላባቸው አጋጣሚዎች ድክመቶቹ ሆነው እንዳይቀጥሉ ያሰጋዋል።

ሙሉ ለሙሉ ለመሆን የተቃረበ የስብስብ ለውጥ አድርጎ ውድድሩን የጀመረው ሀዲያ ሆሳዕና ከዓምናው የተለየ መልክን ተላብሶ ዙሩን አገባዷል። አምና በመከላከል ጥንካሬ አስገራሚ የነበሩት ነብሮቹ ዘንድሮ ግን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ የኋላ መስመር ድክመታቸው ጎልቶ ሲወጣ ተመልክተናል። ይህን በበርካታ ጎሎች የሚያካክስ የፊት መስመር ስኬትን ማስመዝገብ አለመቻሉም ለደረጃው መውረድ አንዱ ምክንያት ነው። እንደ አዲስ ስብስብ መሰል ችግሮች የሚጠበቁ ቢሆንም ቡድኑ ወጥ በሆነ የተጫዋቼች እና የአደራደር ምርጫ መቀጠሉ እንደቡድን ቅርፅ የመያዝ ጊዜው ከታሰበው በላይ እንዳይሆን አስተዋፅዖ አድርጎለታል። በተለይም በሦስት ተከላካዮች በሚጀምረው አደራደሩ ውስጥ የመስመር ተመላላሾቹን በሰው ሜዳ ላይ ገፍተው እንዲጫወቱ በማድረግ እና ከአጥቂዎቹ ውጪ አማካዮችንም ወደ ሳጥን እንዲቀርቡ በማድረጉ ረገድ ጥሩ ፍንጭ የሰጠባቸው ጨዋታዎች ነበሩ።

ዛሬ ምሽት ባስነበብነው ዜና የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በመጠኑ መስመር የያዘላቸው ቡድናቸውን በተጨማሪ ተጫዋቾች ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት በክለቡ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ኃላፊነት እንደማይወስዱ መግለፃቸው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ድል ላልቀናው ቡድናቸው የነገ ከባድ ጨዋታ ጥላ የሚያጠላ ይመስላል። ነገር ግን እንደ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከፍ ባለ ትኩሩት ለተጋጣሚ ቀዳዳ የማይሰጥ አቀራረቡን ከደገመ ከፋሲል ከነማ ከፍ ያለ ተነሳሽለት ሲሆን የማጥቃት ሂደቱ ከሁሉም አቅጣጫዎች አደገኛ ከሆነ ቡድን ጋር የሚገናኙበት ሂደት ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።

በጨዋታው በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም። በለሚ ንጉሴ የመሀል ዳኝነት የሚመራው ይህ ጨዋታ ሶርሳ ዱጉማ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳትነት ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።

የእርስ እርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በሊግ ታሪካቸው ለአራተኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን
ከዚህ ቀደም በተደረጉት ሦስት ጨዋታዎች ፋሲል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ፋሲል አምስት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– ሊጉ ከረጅም ከዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።

ያጋሩ