በከፍተኛ ሊግ መድመቅ የቻለው የመስመር አጥቂ ወደ ባህር ዳር ከተማ አቅንቷል

በዝውውር መስኮቱ የመስመር ተከላካይ ያስፈረመው ባህር ዳር ከተማ አሁን ደግሞ የመስመር አጥቂ ከከፍተኛ ሊግ አግኝቷል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከቀናት በፊት ቡድናቸውን በሁለተኛው ዙር ለማጠናከር በድሬዳዋ ከተማ ውሉ የተጠናቀቀው የመስመር ተከላካይ ሄኖክ ኢሳያስን ማስፈረማቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ በከፍተኛ ሊግ ዘንድሮ ድንቅ እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የመስመር አጥቂው አደም አባስን በውሰት አግኝተዋል።


የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ መካሄዱን ተከትሎ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በየጨዋታዎቹ በመገኘት አደምን እንቅስቃሴ ሲከታተሉት ቆይተው በስተመጨረሻም በውሰት ለመውሰድ ባህር ዳር ለተጫዋቹ ባለ ንብረት ንግድ ባንክ የውሰት ጥያቄ ደብዳቤ አስገብተዋል። ንግድ ባንክም ጥያቄውን ተቀብሎ ዛሬ የህክምና ምርመራ በማድረግ ነገ የመጨረሻውን ጨዋታ ለንግድ ባንክ ካደረገ በኃላ ወደ አዳማ በመምጣት ቡድኑን የሚቀላቀል ይሆናል።


በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የአራት ዓመት ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ20 ዓመት በታች አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የተጫወተው አደም በኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወትም ችሏል። በዘንድሮ ዓመትም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተቀላቀለ ሲሆን ሰባት ጎሎችን አስቆጥሮ ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፏል።