ሲዳማ ቡና አማካይ ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ተስማማ

በትናትናው ዕለት አንጋፋውን አጥቂ ሳልዓዲን ሰዒድ በእጁ ያስገባው ሲዳማ ዩጋንዳዊውን አማካይ ለማስፈረም ስምምነት ፈፅሟል።

በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ቡና በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ተጠናክሮ ለመምጣት በዝውውር መስኮቱ ለመሳተፍ እንቅስቃሴ ላይ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ ተጫዋቹንም በትናንትናው ዕለት የግሉ አድርጓል። አሁን በተገኘ መረጃ ደግሞ ክሪዚስቶም ንታምቢ በሁለተኛው ዙር ቡድኑን ለማገልገል ስምምነት ፈፅሟል።

2009 ላይ በደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደር ከነበረው ቫዝኮ ደጋማ ክለብ ጅማ አባ ቡናን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው የተከላካይ አማካይ በጅማ ለአንድ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ወደ መዲናው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ እንደነበር አይዘነጋም። በቡናማዎቹ ቤትም ለሁለት ዓመታት ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን 2011 ላይ ግን ወደ ሀገሩ በመመለስ ለዋኪሶ ጂያንትስ ፊርማውን በማኖር የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ዓምና ደግሞ ዳግም ወደ ሀገራችን በመመለስ ሰበታ ከተማን አገልግሎ ከወራት በፊት ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከክለቡ መለያየቱ ይታወቃል።

ንታምቢ ከሰበታ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ሳምንታትን አሳልፎ ዳግም ወደ ሀገራችን በመምጣት የፋሲል ተካልኙን አዳማ ከተማ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ ልምምድ ለቀናት ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ሀሳቡን በመቀየር ወደ ሲዳማ ቤት አምርቷል። ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓት ከሲዳማ ጋር የሚገኝ ሲሆን ፊርማውን ለማኖር የስራ ፍቀድ እና ተያያዥ የወረቀት ጉዳዮች ብቻ እንደሚቀሩት የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ኔታምቢ በጅማ አባ ቡና ቆይታው በአሁኑ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ስር መጫወቱ ይታወሳል።