ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን አጠናክሯል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


ከሊጉ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ቀዳሚው 09:00 ላይ ሲደረግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን 3-1 በመርታት መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች አዲስ ፈራሚዎቻቸው ያሬድ ሀሰን እና ቢስማርክ አፒያን በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ በማካተት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4-3-3 ሰበታ ከተማ ደግሞ በ4-1-4-1 ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን እና ቀጥተኛ ጥቃት ከመነሻው መታየት የጀመረበት ጨዋታ ብዙም ሳይቆይ ጎል ተቆጥሮበታል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ የግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ስህተት ታክሎበት ቸርነት ጉግሳ ያመቻቸለትን ፍሪምፖንግ ሜንሱ ግብ አድርጎታል። 

ጊዮርጊሶች በሁለቱ መስመሮች ወደ ሳጥን ከሚያደርሷቸው ኳሶች እና ከቆሙ ኳሶች ጫናቸውን ከፍ አድርገው ቀጥለዋል። የቡድኑ ቀጣይ ሙከራ 15ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በረጅሙ ወደ ግራ በተጣለ ኳስ ቸርነት ጉግሳ አመቻችቶለት አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከዚህ በኋላ ሰበታዎች በግራ ወደ ተሰለፈው ዱሬሳ ሹቢሳ አድልተው ከሜዳቸው መውጣት ጀምረዋል። የቡድኑ ቀዳሚ የማጥቃት ጥረቶች ወደ ግብ ዕድልነት ባይቀየሩም 23ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጌቱ ኃይለማሪያም ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግብ የላከው ኳስ ባህሩ ነጋሽን አልፎ በግቡ ቋሚ ሲመለስ ቢሳማርክ አፒያ ከቅርብ ርቀት ላይ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከውሀ ዕረፍቱ መልስ ጨዋታው ወደ መመጣጠን የመጣ ሲሆን ሰበታዎች ኳስ መስርተው ለመውጣት ጊዮርጊሶች ደግሞ በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ፉክክሩን አድምቆታል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ከሄኖክ አዱኛ የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ አቤል ያለው ጌቱን በድንቅ ሁኔታ በማለፍ ወደ ግብ ሲሞክር ቀጣይዋ ግብ ለመሆን ተቃርባ በሰለሞን ተጨርፋ ወጥታለች። ከሦስት ደቂቃ በኋላ ምላሽ የሰጡት ሰበታዎች ግን ተሳክቶላቸዋል። ከማዕዘን ምት የተነሳውን ኳስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ በአግባቡ ማራቅ ሳይችሉ አግኝቶ በረከት ሳሙኤል ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። በረከት ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ሊያመሩ ሲቃረቡም ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት ሙከራ አድርጎ ለጥቂት ወደ ላይ ተነስቶበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛውም አጋማሽ የመጀመሪያውን ፈጣን አጀማመር ደግመዋል። የቡድኑ የፊት አጥቂ አማኑኤል ከሳጥን ውጪ በቀጥታ በመምታት ሲሞክር በመቀጠል ደግሞ ከቸርነት እና ከየአብስራ የደረሱትን ኳሶች ወደ አደገኛ ዕድልነት ቢቀይርም ግብ መሆን አልቻሉም። 55ኛው ደቂቃ ላይ የአብስራ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ ሌላ ያለቀለት ዕድል ሲፈጥር የቸርነት ጉግሳ ሙከራ ግን ሁለቱን ቋሚዎች ገጭቶ ወጥቷል። የጊዮርጊሶች ጫና ሳይባራ ሲቀጥል ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀይደር ሸረፋ በረጅሙ ወደ ፊት የላከውን ኳስ አማኑኤል አፈትልኮ በመውጣት በግብ ጠባቂው ሰለሞን አናት ላይ በመላክ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ጊዮርጊሶች ከመሩ በኋላ ጫናቸውን ቀነስ አድርጋው ኳስ ወደ መያዙ ሲያመዝኑ ሰበታዎችም ቀስ በቀስ ሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ላይ መታየት ጀምረዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጊዮርጊስ ተቀያሪ ተጫዋቾች ንክኪ ሦስተኛ ጎልን ፈጥሯል። ሱለይማን ሀሚድ ከከነዓን ማርክነህ ተቀብሎ መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ሰለሞን በአግባቡ መቆጣጠር ተስኖት አዲስ ግደይ ግብ አድርጓታል። እንቅስቃሴው ለከነዓን እና አዲስ የመጀመሪያ ንክኪ ነበር።

ከሦስተኛው ግብ በኋላም ሰበታዎች ኳስ መስርተው ወደ ሳጥኑ ለመድረስ ሲጥሩ ቢታዩም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት ይሄዱ የነበሩባቸው ቅፅበቶች ይበልጥ አስፈሪ ሆነው ታይተዋል። በጨዋታው ሌላ ግብ ሳይቆጠር በጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ፈረሰኞቹ ነጥባቸውን 34 በማድረስ ከወላይታ ድቻ ያላቸውን ልዩነት ስድስት ሲያደርሱ ሰበታ በ9 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ ቀርቷል።