የአሠልጣኖች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 ሰበታ ከተማ

የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ መርሐ-ግብር በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (ምክትል አሠልጣኝ)

ስለጨዋታው እና ቡድኑን ስለመራበት መንገድ…?

ውድድሩን ስንጀምር ከሰበታዎች ጋር ነበር የተጫወትነው። የዛኔ የነበረው ውጥረት ትንሽ ከባድ ነበር። ጨዋታውንም 0ለ0 ነበር የወጣነው። አሁንም ስንጀምር ጥሩ አረግን ግን በተወሰነ ትንሽዬ ስህተት ገባብን። ይህ ቢሆንም በጥሩ ነገር እረፍት እኩል ለእኩል ወተን ነበር። እረፍት ላይ ማድረግ ያለብንን እና ማስተካከል ያለብንን ነገር አስተካክለን ውጤቱን ይዘን ወተናል። የሚሳቱን እና አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ ነበር መቁነጥነት ውስጥ የገባሁት።

ከፈጠሯቸው ዕድሎች መነሻነት ስለነበራቸው የአጨራረስ ብቃት?

አጥቂዎቼ ማድረግ የሚገባቸውን አድርገዋል። እንደውም ብዙ ኳሶች ስተናል። መሳት የሌለብንን ኳሶች ራሱ ስተናል። እነዛ ቢገቡ ምን እንደሚፈጠር ማሰብ ነው። ተጫዋቾቼ ግን የፈለኩትን እና የተነጋገርነውን በማድረጋቸው ደስተኛ ነኝ።

ስለቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እና ያለ ዋነኛ አጥቂያቸው አለመጫወታቸው…?

ያሰብኩትን እና የተነጋገርነውን አድርገናል። ስንጀምር ያሰብነውን አድርገውልኝ ነበር። ከዛ በተወሰነ ወረድ ብለው ነበር። እረፍት ላይ ተነጋግረን የተሻለ ነገር አርገውልኝ ውጤት ይዘን ወተናል። አጎሮ ለቡድን ትልቅ አጥቂ ነው። እኔ ግን እንደቡድን ነው የምሰራው። ሁሉም አጥቂዎቼ የተሻለ ነገር እንደሚያደርጉም አውቃለው። ይሄንንም ነገር ሜዳ ላይ አርገውልኛል። ስለዚህ ሁሉም አጥቂዎች አንድ አይነት እና ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ስለጋቶች ብቃት…?

ጋቶች በጣም ጥሩ ነገር ነው ያደረገው። እንዳልኩት ስንጀምር ጥሩ ነበር ከዛ ግን ከ15 እና 20 ደቂቃ በኋላ ወረድ ብለን ነበር። እነዚህን ነገሮች የተፈጠሩበትን ነገር እረፍት ላይ ተነጋግረን ነው በሁለተኛው አጋማሽ እሱም ለተከላካዮቹ በደንብ ሽፋን ሰጥቶ የተጫወትነው። በአጠቃላይ በተነጋገርነው መሠረት ለቡድኑም ሆነ ለተከላካይ መስመሩ ጥሩ ጉልበት ነው የሰጠው።

ብርሃን ደበሌ – ሰበታ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ)

ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የዛሬው ጨዋታ አስፈላጊነት?

የዛሬውን ጨዋታ በጣም ፈልገነው ነበር። እግር ኳስ ደግሞ ሂደት ይፈልጋል። እኛ የተዘጋጀነው በአነስተኛ ሁኔታ ነበር። ከዚህ አንፃር በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሆነ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተገዳደርንበት ጨዋታ አሳልፈን ነበር። በዚህም አንድ ለአንድ እረፍት ወተናል። ይሁን እና በሁለተኛው አጋማሽ በተከላካዮቻችን ስህተት በተቆጠሩብን ሁለት ጎሎች ለመሸነፍ ችለናል። ለቀጣይ ይሄንን ስህተታችንን አርመን ወደ ተሻለ ነገር ለመምጣት እንዘጋጃለን የሚል እምነት አለኝ።

ስለተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ…?

የመጀመሪያውን 15 እና 20 ደቂቃዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ነግሬያቸው ነበር። በዛች ሰዓት የገባብን ጎል ተጫዋቾቼን ትንሽ የረበሸ ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት ቡድኑ የመጫወት ነገሩ ትንሽ የመዳከም አዝማሚያ ታይቶበት ነበር። ዞሮ ዞሮ ይህ እግር ኳስ ነው። እንቀበለዋለን።

በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጓቸው ለውጦች?

ግቦቹ ከተቆጠሩብን በኋላ የግድ ግብ ማስቆጠር ይኖርብን ነበር። ለውጡንም ያረግነው ከፊት ያሉ ተጫዋቾችን ለማጠናከር እና ጎሎችን ለማግኘት ነበር።

ያጋሩ