ሀዋሳ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር በሦስተኛነት ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ፈራሚዎችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ መሪነት የ2014 የውድድር ዘመንን እየተጓዘ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ሊጉን ያገባደደ ሲሆን የሁለተኛውን ዙር የፊታችን ቅዳሜ ጅማ አባ ጅፋርን በመግጠም ጉዞውን የሚጀመር ይሆናል፡፡ ቡድኑ በዚህኛው ዙር ተጠናክሮ ለመቅረብ ሁለት የተከላካይ ስፍራ ተጫዋችን በዛሬው ዕለት በይፋ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገር ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜግነት ያለው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ዳርለስ ካሎንጂ ኃይቆቹን የተቀላቀለው ቀዳሚው ፈራሚ ሆኗል፡፡በሀገሩ ለሚገኙት አራት ክለቦች ኢስቶይል ዲ ኮንጎ ፣ ካራ ብራዛቪል ፣ ኤ ኤስ ቪታ እና ዲያቭልስ ኖይል ግልጋሎት የሰጠው ይህ የ27 ዓመት ተጫዋች ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ወደ ሞሪታኒያ ፕሪምየር ሊግ በመጓዝ ኖሀ ዳሂቡ በተባለ ክለብ ቆይቶ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመምጣት ሀዋሳ ከተማን በዛሬው ዕለት ፌድሬሽን በመገኘት በአንድ
ዓመት ውል መቀላቀል ችሏል፡፡

ሁለተኛው ፈራሚ አቤኔዘር ኦቴ ነው፡፡እግርኳስን በትውልድ ሀገሩ ጅንካ ከተማ የጀመረው የቀድሞው የኢኮስኮ ፣ ወልቂጤ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜ እንዲሁም ዘንድሮ ደግሞ በስልጤ ወራቤ ያለፉትን ስድስት ወራት ሲጫወት የቆየው የግራ መስመር ተከላካዩ በይፋ ሀዋሳን በዛሬው ዕለት በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ኮንትራት ተቀላቅሏል፡፡

ያጋሩ