“ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ የማያውቅ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ተጫዋቾቼ በዓለም ዋንጫውም ትልቅ ቦታ ላይ አድርሰውን ስላለፉ ከልብ አመሰግናለሁ” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


የኢትዮጵያዊ የሴቶች ከ 20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሴካፋ ቻምፒዮኑ የኢትዮጵያዊ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ቡድኑ ባሳለፍነው እሁድ በመጨረሻው የማጣሪያ ግጥማያ በጋና ከተረታ በኋላ ልዑካን ቡድኑ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰ ሲሆን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የመጨረሻውን ጨዋታ እና አጠቃላይ የቡድኑን የማጣሪያ ጉዞ የተመለከተ መግለጫ ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሰጥተዋል።

በመግለጫው መጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር በጋና ጥሩ ቆይታ እንደነበራቸው እና የማሸነፍ ዕድላቸው ሰፊ እንደነበር የገለፁት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ቡድናቸው ውጤቱ የተበላሸበት በመጀመሪያው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በመሆኑ “የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል። አሰልጣኙ በመልሱ ጨዋታ ቡድኑ ከጋና የተሻለ መንቀሳቀሱን ያወሱ ሲሆን በሴካፋ እስከ ቻምፒዮንነት በዓለም ዋንጫ ማጣሪው ደግሞ እስከ መጨረሻ ጨዋታ ለተጓዘው ቡድናቸው እንዲህ በማለት ምስጋና አቅርበዋል። ” ከሴካፋ እስከ ዓለም ዋንጫው ድረስ እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች ሀገራቸውን በተሻለ መልኩ አገልግለው ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ የማያውቅ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ተጫዋቾች እንደመሆናቸው መጠን በዓለም ዋንጫውም ትልቅ ቦታ ላይ አድርሰውን ስላለፉ ተጫዋቾቼን እጅግ በጣም ከልብ አመሰግናለሁ።” አሰልጣኝ ፍሬው ከተጨዋቾቻቸው በተጨማሪ ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ፣ ለፌዴሬሽኑ እንዲሁም ‘ለደገፉን እና ለነቀፉን ሁሉ’ በማለት ምስጋና አቅርበዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው በመጪዎቹ ጊዜያት የተሻሉ ቡድኖችን ለመገንባት በወጣቶች ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን በማብራራት መግለጫቸውን አጠቃለዋል። በማስቀጠል አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በጋናው ጨዋታ ቡድኑ ስለተሻሻለባቸው ነጥቦች

“እዚህ በ45 ደቂቃ ሦስት ጎል ገብቶብናል። በጣም የትኩረት ችግር ነበረብን። ጎሎችን ማግባት አልቻልንም ፤ የተሻሉ ዕድሎችን ብንፈጥርም። የሜዳ እና የደጋፊ አድቫንቴጅም አልወሰድንም። ልጆቻችን በደጋፊ መሀል ተጫውተው የሚያዉቁ አይደሉም ፤ እሱም አንድ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በሥነልቦናው ብዙ ነገሮችን አርመን ነው የሄድነው። እዛ የተሻልን ያደረገን እዚህ ከነበረው በተሻለ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ጥሩ የኳስ ቁጥጥሩን አድርገን ነው የወጣነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ሁለቴ ደርሰው ሁለት ግብ ማስቆጠራቸው ነው። ከዛ በተቀረ ያደረጉት አስደንጋጭ ነገር አልነበረም ፤ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እንደመጫወታቸው። ደጋፊው እንደውም እኛን ሲደግፍ ነበር እውነት ለመናገር። የሚያስቆጩ ኳሶችንም ስተናል። ትክክለኛ ጎልም አስቆጥረናል ፤ ቫር ቢኖር ኖሮ እንደውም ተጠቃሚ እንሆን ነበር። የሰው ልጆች ደግሞ በስህተት የታጀብን ነን። ዳኞች ከማወቅ ካለማወቅ የሚሳሳቱት ነገር አለ ፤ ትክክለኛ የተቆጠረ ጎል ነበረን። ደጋፊውም ያመነበት ጭምር ነበር።”

በጋና ቆይታቸው ስለወሰዱት ልምድ

“ምዕራብ አፍሪካዎቹን ባላቸው ስም ነው እንጂ እያከበርናቸው ያለነው ምንም ከእኛ የተሻለ ነገር አላየሁባቸውም። እስከዛሬ በተወዳደርኩት ውድድር የከበደኝ የምስራቅ አፍሪካ ነው። ካየሁት ቡድን እንደውም ጠንካራው ታንዛኒያ ነው። ለሁሉም በድኖች ክብር ቢኖረኝም ግን የጋናን ቡድን እንደ ታንዛኒያ ይከብዳል ብዬ መናገር አልችልም። የጋና ቡድን ከእኛ የተሻለ ምንም ነገር ያላየሁበት ነው። እግርኳሳቸውን ግን በሲስተም ነው የሚመሩት ፤ እጅግ በጣም በተሻለ ሁኔታ ለሴቶች ትኩረት ሰጥተው ነው የሚሰሩት ፤ ትልቁ ለውጥ ይህ ነው። ከዛ ውጪ ምስራቅ አፍሪካ ላይ እንዳየሁት የሴቶች ሊጋቸው በሚዲያ ሁላ ይተላለፋል። የሚዲያ አካላት ተጫዋቾቻቸውን በጣም ነው የሚያነሱት ፤ እጅግ በጣም ጥሩ አድርገው። እዛ ሀገር ለሴቶች እግርኳስ ጋዜጠኛው ራሱ ትልቅ መስዕዋትነት ነው የሚከፍለው። ባለሙያ በጣም ነው የሚያከብሩት ፣ ተጫዋቾችንም በጣም ነው የሚያከብሩት ፤ እጅግ በጣም። በየሄድኩበት ይህንን አይቻለሁ። ታንዛኒያ ፣ ዩጋንዳ ፣ ቦትስዋና ለሴት ለወንድ አይሉም።”

አሰልጣኙ ከዚህ በተጨማሪ ጋናዊያን ደጋፊዎች ለኢትዮጵያ የሰጡትን ድጋፍ እንዳስገረማቸው እነሱም አፍሪካን ወክለው የሚሄዱ በመሆናቸው ”እንኳን ደስ ያላችሁ” ማለታቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የሴቶች ሊግ የቴሌቭዢን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱ ለተጨዋቾች የውጪ ዕድል እንደሚያመጣ ያነሱ ሲሆን በቀጣይ በፌዴሬሽኑ የፓይለት ፕሮጀክቶች ፣ የክልል ውድድሮች እንዲሁም ክለብ የሌላቸው ተጫዋቾችን ጭምር በመመዘን እና በመመልመል ላይ መስራት እንደሚያስቡ ተናግረዋል።