ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

በቡና ስም የሚጠሩት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉትን የነገ ቀዳሚ ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።

ዛሬ ጅማሮውን ያደረገው የሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ነገ ቀጥሎ ሲከናወን 9 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡናን ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኛል። ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ (አንድ ጨዋታ የበለጠ አድርጎ) በሦስት ጨዋታዎች በሚገኝ ድል ነጥብ ብቻ ተበልጦ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ያሳየውን ጠንካራ ብቃት በሁለተኛውም ዙር ጅማሮ በመድገም እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ነገ ጥረቱን እንደሚቀጥል ይታመናል። በተቃራኒው በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ካጋጠማቸው የውጤት ማጣት ጉዞ በማገገም ሁለተኛውን ዙር በድል ለመጀመር ብርቱ ትግል እንደሚያደርጉ ይገመታል።

ከዓምናው አስጊ ጉዞ ትምህርት በመውሰድ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ራሱን በሚገባ አጠናክሮ ውድድሩን የጀመረው ሲዳማ በውጤትም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ እንደነበር ተመልክተናል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከስሩ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ጋር በጣምራ በሊጉ ትንሽ ጨዋታዎች የተሸነፈው ሲዳማ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ካለው የተጫዋች ክምችት መነሻነት በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት 2 ተጫዋቾችን ብቻ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ክለቡ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ ውስጥ ያለ አጥቂ ቢኖረውም (ይገዙ ቦጋለ) አንጋፋውን ጨራሽ አጥቂ ሳልዓዲን ሰዒድ በትናንትናው ዕለት አስፈርሟል። ከወገብ በላይ ከሚገኙ ተጫዋቾቹ ወጣትነት ጋር ተያይዞ ሳልዓዲን መምጣቱ በልምድ ረገድ የሚጨምረው አንዳች ነገር እንዳለ ሲታሰብ በአብዛኛው ይገዙ ላይ የተንጠለጠለውን የግብ ማስቆጠር ሀላፊነትም ሳላዓዲን ለማቃለል እንደሚረዳ ይገመታል። ሌላው የክሪዚስቶም ንታምቢ ግዢ በስብስቡ ውስጥ ካለው የአማካይ ተጫዋቾች ክምችት አንፃር ብዙም ግልፅ ባይሆንም በቦታው ጥራት እና ብዛት መኖሩ ለፉክክር የሚጠቅም መሆኑ አይካድም።

ከሲዳማ በተቃራኒ ከዓምናው ምርጥ ብቃቱ በተለየ መንገድ እየተጓዘ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮውን የውድድር ዓመት የጀመረበትም ሆነ ያገባደደበት መንገድ ለትችት የሚዳርገው ነው። ከአቤል እንዳለ ውጪ ከወገብ በላይ በሚገኝ ቦታ ግዢ ሳይፈፅም ዓመቱን የጀመረው ክለቡ የቀደመ ጠንካራ ጎኑ የነበረው የግብ ዕድሎችን የመፍጠር እና እነርሱንም የመጠቀም ብቃቱ እጅጉን ወርዷል። በመጀመሪያው ዙርም በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙት ክለቦች ውጪ ሦስተኛው አነስተኛ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ያደረገ (110) እንዲሁም ሁለተኛው ጥቂት ግቦችን ያስቆጠረ (11) ክለብ ነው። ይህንን ጎል ፊት ያለ መሳሳት ለማጠናከርም በዝውውሩ ተመስገን ገብረኪዳንን አስፈርመዋል። እንደ ዓምናው አይሁን እንጂ አሁንም በአቡበከር እግሮች ጥገኛ የሆነው ክለቡንም የግብ አማራጭ የሚሰት ተጫዋች ማግኘቱ መልካም ነው። በተለይ በሊጉ ከጅማ ጋር እኩል በጥቂት ተጫዋቾች (5) ብቻ ግብ ያገኘ ክለብ በመሆኑ አማራጩን ማስፋት የግድ ይለው ነበር።

በ7ኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ ከደረሰበት የ4ለ0 ድል ውጪ በአንድ ጨዋታ ብቻ 2 ግብ ያስተናገደው የሲዳማ የኋላ መስመር ነገም ለቡና ተጫዋቾች ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል። በተቃራኒው ቡናዎችም የጨዋታውን የኳስ ቁጥጥር በእጃቸው በማስገባት በትዕግስት በሮችን ከየአቅጣጫው ለማንኳኳት እንደሚውተረተሩ እሙን ነው። ሲዳማም ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ የማጥቃት ሀሳብ ወደ ሜዳ ይዞ እንደሚገባ ሲጠበቅ የቡናን የኳስ ምስረታ በማጨናገፍ የጎል ማግባት አጋጣሚ ብዙም ከግቡ ሳይርቅ ለማግኘት እንደሚያስብ ይገመታል። ከዚህ ውጪ ከመጨረሻዎቹ ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በማሸነፍ በድምቱ ሦስት ግብ ብቻ ያስቆጠረው የአሠልጣኝ ካሣዬ ስብስብ ነገ በማጥቃቱ ረሀድ ቁርጠኛ ሆኖ ሊገባ እንደሚችልም ይታሰባል።

ሲዳማም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ የሚያጡት ተጫዋች የለም። ፍሬው ሰለሞን ግን በግል ጉዳይ ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ሆኗል። አሠልጣኝ ገብረመድህን የሳልዓዲንን ዝውውር ቢያገባድድም ክለቡ በቀድሞ ወጌሻው በተላለፈበት ዕግድ የተጫዋቹ የመጫወቻ ፍቃድ (ቴሴራው) ስለተያዘ ነገ አይጠቀሙበትም። የኢትዮጵያ ቡና አዲሱ ብቸኛው ተጫዋች ተመስገን ገብረኪዳን ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተመላክቷል።

ጨዋታውን ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ለዓለም ዋሲሁን እና ማህደር ማረኝ በረዳት እንዲሁም በላይ ታደሠ በአራተኛ ዳኝነት ይሰየማሉ።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 23 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 8ቱን የማሸነፍ የብልጫ ታሪክ አለው። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ 7ቱን ሲረታ ቀሪውን 8 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት አገባደዋል።

በ23ቱ ግንኙነት ግን ብዙ ግቦችን ያስቆጠረው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ነው። በዚህም ቡና 31 ሲዳማ ደግሞ 27 ኳሶችን ከመረብ ጋር አዋህደዋል።

– ሊጉ ከረጅም ዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።