ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዩ ዳሰሳ ተሰናድቷል።

አዲስ አበባ ከተማ ካለበት አስጊ ቀጠና ፈቅ ለማለት እና ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ያገኛትን ብቸኛ ድል ለመድገም እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከመሪዎቹ ላለመራቅ እና እንደ መጀመሪያው ዙር ይሄንንም ጨዋታ በአሸናፊነት ለመጀመር የሚደርጉት የነገ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ውድድሩን ጀምሮ በአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ ዙሩን ያገባደደው አዲስ አበባ ከተማ ከሚያሳየው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር የሚያገኘው ውጤት በመጠኑ ገላጭ እንዳይደለ ብዙዎች ይስማማሉ። ለቀጥተኛ አጨዋወትም ሆነ ኳስን ይዞ በማንሸራሸር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚሆኑ ተጫዋቾች የያዘው ቡድኑ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል እየደረሰ ዕድሎችን ለመፍጠር ባይቸገርም በውሳኔ አሰጣት እና የስልነት ችግሮች ካደረጋቸው 131 አጠቃላይ የግብ ማግባት ሙከራዎች 54ቱን ዒላማውን በማስጠበቅ ወደ ጎልነት የቀየረው 16ቱን ብቻ ነበር። ካለው ስብስብ አንፃር እና እንደ አዲስ አዳጊ ቡድን በዚህን ያህል ደረጃ ለተቃራኒ ግብ ቅርቡ መሆኑ ቢያስደንቀውም እንደተባለው የአጨራረስ ብቃቱ ላይ መስራት ያስፈልገዋል። የመጨረሻው የሜዳ ሲሶ ላይ ጥራት ለመጨመር የአጥቂ አማካዩ ኤሊያስ ማሞን ወደ ስብስቡ ቢቀላቅልም ከህክምና ጋር ተያይዞ ተጫዋቹ ከትናንት በስትያ ቡድኑን ተሰናብቷል። ከዚህ ውጪ ተስፈኛው አጥቂ መሐመድ አበራ በቦታው መፍትሔ ለመስጠት ደርሷል።

አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን በመንበሩ ሾሞ የዘንድሮውን ውድድር የጀመረው ባህር ዳር ከተማ በብዙዎች ዘንድ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን ቢታመንም እኩል አምስት ጨዋታዎችን አሸንፎ፣ ተሸንፎ እንዲሁም አቻ ወጥቶ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ በዓመቱ መጀመሪያ ማግኘት ከሚገባው 9 ነጥብ 7ቱን አሳክቶ ውድድሩን ቢጀምርም ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ መጥቷል። እርግጥ በስብስብ ደረጃ በየመጫወቻ ቦታው ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ቢይዝም ከጉዳት እና ቅጣት ጋር ተያይዞ መሳሳት አጋጥሞት ሲቸገር ነበር። በተለይ ከመጨረሻዎቹ 8 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፉን እና በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አጥጋቢ አለመሆኑ ሲታወስ በሁለተኛው ዙር ትልቅ ስራ እንደሚጠብቀው ይታመናል። መጋቢት 3 በመቀመጫ ከተማው ወደ ዝግጅት የገባው ክለቡም በዝውውር መስኮቱ ሔኖክ ኢሳይያስን የግሉ አድርጓል። በመስመር ተከላካይ እና አማካይ እንዲሁም በመሐል ሜዳ ተጫዋችነት ለቡድኑ አማራጭ እንደሚሰጥ የሚታሰበው ሔኖክ በቶሎ ከአጋሮቹ ጋር ከተዋሐደ ተፅዕኖውን ለማሳረፍ ጊዜ እንደማይፈጅ ይታሰባል። እንዳልነው የጉዳት እና የቅጣቱ ጉዳይ ግን አሁንም በወሳኝ ተጫዋቾቹ ላይ መኖሩ በልበ ሙሉነት ጨዋታውን በቀላሉ ሊወጣ ይችላል እንዳንል ያደርገናል።

እኩል 16 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩት ሁለቱ ክለቦች ሁሉን አስማሚ አስተማማኝ እና ወጥ ብቃት ላይ ባለመገኘታቸው ነገ ጠንክረው ጨዋታውን እንደሚቀርቡ እና ወደ ድል ለመመለስ እንደሚጥሩ እንዲገመት አድርጓል። ይህንን ተከትሎም ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ሊከተሉ ይችላሉ። ከጅማ በመቀጠል ብዙ ጨዋታዎችን የተረታው አዲስ አበባ ከተማ ከወገብ በላይ የሚገኙትን የባህር ዳር ተጫዋቾች መቆጣጠሪያ ሁነኛ መፍትሄ መዘየድ ይገባዋል። በተቃራኒው ባህር ዳርም ፈጣኖቹን አጥቂዎች ጠንካራ ጎን ማምከኛ ብልሀት ሊገባው ግድ ይላል። ከዚህ ውጪ ሁለቱም ክለቦች ከኳስ ጋር ማሳለፍ የሚፈልጉ በመሆኑ ሳቢ እና ከሳጥን ሳጥን የማያቋርጥ እንቅስቃሴ እንደሚያስመለክቱ ቀድሞ መናገር ይችላል።

አዲስ አበባ ከተማ በነገው ጨዋታ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጼጥሮስን አያሰልፍም። በልምምድ ላይ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አማካዩ ቻርለስ ሪባኑ የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም አሁን ከመሸ ባገኘነው መረጃ ተጫዋቹ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተረጋግጧል። ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ዋነኛ አጥቂው ኦሴ ማውሊ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ግልጋሎቱን አያገኝም። ከማውሊ ጉዳት ውጪ መናፍ ዐወል፣ አህመድ ረሾድ እና ግርማ ዲሳሳ በቅጣት አይኖሩም።

12 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ፍልሚያ ባህሩ ተካ ከረዳቶቹ ሸዋንግዛው ተባበል እና ባደታ ገብሬ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛዋ ሊዲያ ታፈሰ ጋር በመሆን እንደሚመሩት ለማወቅ ችለናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አዲስ አበባ እና ባህር ዳር በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ዘንድሮ ነው። በዚህም በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 በተደረገው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በተመስገን ደረሰ አንድ እንዲሁም በኦሴ ማውሊ ሁለት ግቦች ሦስት ለምንም አሸንፎ ነበር።

– ሊጉ ከረጅም ዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።

ያጋሩ