አዲስ አበባ ከተማ ከአዲስ ፈራሚው ጋር ሲለያይ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የመዲናው ክለብ ከቀናት በፊት ወደ ስብስቡ ከቀላቀለው ኤሊያስ ማሞ ጋር ሲለያይ ሁለት ተጫዋቾችን ደግሞ አስፈርሟል።

በአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ በመጣበት ዓመት ላለመውረድ በአቅሙ በአጋማሽ የዝውውር መስኮት ለመሳተፍ ጥረት ሲያደርግ ሰንብቷል። ከጋብሬል አህመድ እና ያሬድ ሀሰን ጋር በስምምነት የተለያየው ክለቡም መሐመድ አበራን እና ኤሊያስ ማሞን ወደ ስብስቡ እንደቀላቀለ ቀደም ብለን መግለፃችን ይታወቃል። ባለ ልምዱ ኤሊያስ ማሞ ግን አጋሮቹን ተቀላቅሎ ልምምድ ለቀናት ከሰራ በኋላ ከህክምና ጋር ተያይዞ ከሁለት ቀናት በፊት ቡድኑን እንደተለያየ ለማወቅ ችለናል።

በዛሬው ዕለት የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ከባህር ዳር ከተማ ጋር የሚያደርገው ቡድኑ ከመከላከያ ጋር የተለያየው ተስፈኛውን ተጫዋች አቤል ነጋሽን አግኝቷል። በመከላከያ ከእድሜ እርከን ቡድኖች ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን የተጫወተው አቤል የ6 ወር ውል ቢኖረውም የአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ስብስብ በስምምነት ለቆ መዳረሻውን አዲስ አበባ አድርጓል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የውድድር ዓመቱን በከፍተኛ ሊግ ያሳለፈው አዩብ በቀታ ነው። አዩብ ከዚህ ቀደም በሀላባ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጫውቶ አሳልፎ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ወደ ሀላባ ዳግም በመመለስ ድንቅ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ አሳልፎ ነበር። አሁን ደግሞ በውሰት የመዲናውን ክለብ ተቀላቅሎ እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ ግልጋሎት የሚሰጥ ይሆናል።

ያጋሩ