ከደቂቃዎች በፊት ይፋ በሆነው የፊፋ የሀገራት ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ደረጃዎችን ሸርተት ብሏል።
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ በየወሩ የአባል ሀገራቱን ደረጃ በድረ-ገፁ ይፋ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ተቋሙ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የ211 ሀገራትን ደረጃ ይፋ ሲያደርግም ለበርካታ ወራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ቤልጂየም ደረጃዋን ለብራዚል አስረክባ ወደ ሁለተኛ ሸርተት እንዳለች ታውቋል። ከብራዚል እና ቤልጂየም በመቀጠል ደግሞ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለክብር ፈረንሳይ ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች። ከአህጉራችን አፍሪካ ደግሞ ሴኔጋል፣ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ ከዓለም 20፣ 24 እና 30ኛ ደረጃን በመያዝ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ቦታን ተቆናጠዋል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ በየካቲት ወር በ1081.24 ነጥቦች 138ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን በመጋቢት ወር ግን የ4.57 መቀነስ አስመዝግቦ በ1076.67 አጠቃላይ ነጥቦች 140ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ብሔራዊ ቡድናችን ከአህጉራች አፍሪካ ደግሞ 42ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተመላክቷል።
ከስድስት ቀናት በፊት በወጣው የእንስት ብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ ደግሞ ሉሲዎቹ 1124.31 ነጥቦች 123ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው ታውቋል።