“እንደማልመለስ አድርጌ እንዳስብ የሚያደርጉ ስሜቶች ይመጡብኝ ነበር” – አዲስ ግደይ

ከከባድ ጉዳት እና ከረጅም የማገገሚያ ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ግቦችን ማስቆጠር ከጀመረው አዲስ ግደይ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

ከሲዳማ ቡና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማቅናት በ2013 በሁለት ዓመት ኮንትራት ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው አዲስ ግደይ ከጉዳት ጋር በተያያዘ የታሰበውን ግልጋሎት ሳይሰጥ ቆይቷል። የዋልያዎቹ የመስመር አጥቂ የነበረው አዲስ ግደይ ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ መጋቢት ወር ላይ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ወቅት Anterior cruciate ligament እና meniscus ተብሎ በህክምና የሚጠራውን ጉዳት አስተናግዶ ቀዶ ጥገና በማድረጉ ለረጅም ወራት ከሜዳ ርቆ ቆይቷል።

መሰል ከባድ ጉዳቶች የተጫዎቾችን የእግርኳስ ህይወት እስከወዲያኛው የማስተጓጎል አቅም አላቸው። እንደ አዲስ ግደይ አዲስ ክለብ ለቀየረ እና ራሱን በማደላደያ ጊዜ ላይ ለነበረ ተጨዋች ደግሞ ይህ አጋጣሚ የሚያመጣውን ፈተና ይበልጡኑ ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው። ተጨዋቹ በዚህ ዓመት ከጉዳቱ አገግሞ ከቡድኑ ጋር ልምምድ መጀመሩ ከተሰማ ጊዜያቶች ቢያልፉም ወደ ጨዋታ ተመልሶ ከግብ አስቆጣሪነቱ ጋር የሚገናኝበት ጊዜ ቅርብ አይመስልም ነበር። አዲስ ከባዱን ጊዜ ስላለፈበት ሚስጥር ሲናገር “መጀመርያ ሰሞን ህመሙ አዕምሮህ ላይ ተፅዕኖ ስለሚፈጥር ተስፋ የሚያስቆርጡ እና እንደማልመለስ አድርጌ እንዳስብ የሚያደርጉ ስሜቶች ይመጡብኝ ነበር። ግን ወድያው ከዚህ ስሜት የምወጣበትን ነገር ነው የማደርገው። በዙርያዬም ያሉ ሰዎችም እንደምመለስ በተደጋጋሚ ስለሚነግሩኝ እና እንደኔ ያለ ጉዳት የገጠማቸው ልጆች ጋር እደዋወል ስለነበር በአካልም መጥተው በሚጠይቁኝ ሰዓት የሚነግሩኝ ነገር ያበረታኝ ስለነበር ነው። እንደዚህ ተመልሼ እንደምጫወት የሚነግሩኝ ምክር ይበልጥ መጫወት እንደምችል እንዳስብ እጅጉን ረድቶኛል።” ይላል።

አዲስ ከከባዱ ጊዜ የተመለሰበት መንገድ ግን ጥቂት ደቂቃዎች ሜዳ ላይ በማሳለፍ የጀመረ አልነበረም። በሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከአዲስ አበባ ከተማ ሲገናኙ አዲስ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ ገብቷል። በጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ አጥቂው ለፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት ሲሆን ሌላ አንድ ግብ በማስቆጠር ምልሰቱን አድምቋል። ከዕረፍት በኋላ ሊጉ በሁለተኛው ዙር ሲቀጥል ደግሞ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን በረታበት የትናንቱ ጨዋታም ተቀይሮ በመግባት በመጀመሪያ ንክኪው ጎል ማስቆጠር ችሏል። በቀጥታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲገባ ለአዲስ ቀላል አልነበረም። “አዎ ጫናዎች ነበሩ ያም ቢሆን ልምድ ያለኝ ተጫዋች መሆኔ እና ውስጤ የጤንነት ስሜት እየተሰማኝ በመሆኑ ክለቡም በኮቪድ ምክንያት የተጫዋች ዕጥረት ገጥሞት የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኃላፊነት መውሰድ ስላለብኝ ፍርሀቱን ተቋቋሜ ውስጤን አሳምኜ ገብቻለው።”


በእግርኳስ ህይወቱ ረጅም ጊዜ ከሜዳ የሚያርቅ ጉዳት ከዚህ ቀደም አጋጥሞት የማያውቅ በመሆኑ በጣም ፈታኝ ጊዜ እንዳሳለፈ የሚናገረው አዲስ ቀዶ ጥገናውን ካደረገ በኋላ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ፕሮግራም በአግባቡ መከታተሉ ለማገገም እንደረዳው ይገልፃል። ከዚህ ጋር አያይዞ በዙሪያው የነበሩትን ሲያመሰግን እንዲህ ይላል “ከፈጣሪ ቀጥሎ ከክለቡ አመራሮች ጀምሮ በዙሪያዬ የነበሩ መልካም ሰዎች ፣ የቡድን አጋሮቼ እና በሥነ ልቦናው በኩል ድጋፍ ያደረጉልኝ በተመሳሳይ ጉዳት ውስጥ ያለፉ ተጫዋቾች ከባዱን ጊዜ አሳልፌ ተግቼ በመስራት ወደምወደው እግርኳስ እንድመለስ ስለረዱኝ አመሰግናለሁ።”


ምልሰቱ መልካም የሆነለት አዲስ ግደይ ከፊቱ ቀጣይ ፈተናዎች ይጠብቁታል። እንደቡድን እና በተጨዋቾች የተናጠል ብቃት ጥሩ ጊዜ ላይ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ የቀዳሚ ተሰላፊነትን ቦታ ማግኘት ፣ በሲዳማ ቡና ቤት ነበረውን ግርማ ሞገስ መልሶ ማግኘት ወደ ቁልፍ ተጫዋችነት መመለስ እና ዳግም በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ መመረጥ መቻል በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። ይህንን ለማሳካትም በዘንድሮው የሊጉ መረሐግብር የሚቀሩት 14 ጨዋታዎች የአዲስን ቀጣይ መንገድ እንደሚያመላክቱ ይጠበቃል።