ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በመሀሪ መና እና አቡበከር ናስር ግቦች 1-1 ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን በቀዳሚ አሰላለፋቸው ሳያካትቱ ጀምረዋል።

ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር እና የሲዳማዎች በፍጥነት ወደ ጎል የመድረስ ጥረት የጀመረ ነበር። በቀዳሚው የጨዋታ ክስተት 6ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከብሩክ ሙሉጌታ የደረሰውን ግሩም ተከላካይ ሳንጣቂ ኳስ ተቆጣጥሮ ቢያስቆጥርም በተሳሳተ የጨዋታ ውጪ ውሳኔ ተሽሮበታል።

በሁለቱም በኩል ወደ ግራ መስመር ያደላው የማጥቃት ሀሳብ በዚሁ አቅጣጫዎች በተሰለፉት በአቡበከር ናስር እና ሀብታሙ ገዛኸኝ የግብ ሙከራዎች ይበልጥ ጎልቶ ይታይ ነበር። በኳስ ቁጥጥር በተሻለ ሁኔታ ከሜዳቸው ሲወጡ የነበሩት ቡናዎች ቀጣዩን ለግብ የቀረበውን ከባድ ሙከራ አድርገዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ዊሊያም ሰለሞን ሮቤል ተክለሚካኤል በቄንጥ የሰጠውን ኳስ ከገፋ በኋላ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል።


ጨዋታው ወደ ውሀ ዕረፍት ሊያመራ ሲል ሲዳማዎች በሚነጥቁበት ቅፅበት በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ኳስ ወደ ግራ ይልኩ የነበረበት አጋጣሚ ግብ አስገኝቶላቸዋል። 26ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ ላይ ከአቡበከር ናስር ያጨናገፉት ኳስ በቡና ጎል የቀኝ ክፍል ላይ ሀብታሙ ተቆጣጥሮ ለፍሬው አቀብሎ ፍሬው ሲያመቻችለት መሀሪ መና መሬት ለመሬት በመምታት አስቄጥሯል። ሆኖም ኢትዮጵያ ቡና 31ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር በሲዳማ ሳጥን የግራ ጠርዝ ላይ ባስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችሏል።

በቀሪው የአጋማሹ ክፍለ ጊዜም ጨዋታው በማራኪ ፉክክር ሲቀጥል የኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ ፍሰት ክፍተቶችን የሚፈጥርባቸው ቅፅበቶች ሲቀንሱ ሲዳማዎች ከፈጣን ሽግግር እና ከቆመ ኳስ መነሻ በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ ቀርበው ነበር። 40ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከመሀል ወደ ግራ የጣለውን ኳስ በድጋሚ ከሀብታሙ ተቀብሎ ያደረገው ሙከራ በአቤል ማሞ ጥረት ድኗል። 43ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሰጥኑ መግቢያ ላይ የተነሳውን የዳዊት ተፈራን የቅጣት ምት አቤል ሲመልስ መሀሪ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችልበት ዕድል ቢያገኝም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል።

ኃይል የቀላቀለ ሆኖ በጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥራቸው ሲዳማ ሳጥን ዙሪያ እየደረሰ ወደ ዕድልነት ሳይቀየር ሲቆይ በተመሳሳይ ሲዳማዎችም በሚነጥቋቸው ኳሶች ወደ ፊት የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች አደጋቸው ቀንሶ ነበር። ቀዳሚው ሙከራ 56ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ኃይሌ ገብረትንሳይ በቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ልኮ ሲመለስበት ድጋሚ ያደረገው ሙከራ በተክለማሪያም ሻንቆ ድኗል። ቀስ በቀስ ኳስ ነጥቀው ወደ ፊት ሲሄዱ ማስፈራት የጀመሩት ሲዳማዎች ለሁለተኛ ግብ የቀረቡበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። 66ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ ፈጣን ሽግግር ፍሬው ሰለሞን ከቀኝ መስመር በላከው ኳስ ይገዙ ቦጋለን ከግብ ጠባቂ ጋር ቢያገናኘውም የይገዙ ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል።

ጨዋታው በሁለቱ ሙከራዎች ቢነቃቃም የሜዳ ላይ ግጭቶች እና የተጫዋቾች ጉዳት እያቀዘቀዘው ቀጥሏል። በቀሪ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ መሀል አጥቂነት የተቀየረው አቡበከርን ማዕከል ባደረጉ ቅብብሎች ሲዳማዎች ደግሞ ከቡና ተከላካዮች ጀርባ መግባትን ያለሙ ኳሶችን በመላክ የአሸናፊነት ግብ ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው የጨዋታ ማብቂያ ፊሽካ ሲዳማ ቡናዎች የቅጣት ምት አግኝተው ለመምታት በመዘጋጀት ላይ ሳሉ መነፋቱ የቡድኑን አባላት ያበሳጨበት አጋጣሚ የመጨረሻው ትኩረት ሳቢ ቅፅበት ሆኖ አልፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ26 ነጥቦች የነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ኢትዮጵያ ቡና በ21 ነጥቦች ከ8ኛ ወደ 7ኛ ከፍ ብሏል።