የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

በዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው እና ሲዳማ ቡናን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“ከታክቲካል ትግበራ አንፃር የተዋጣለት አልነበረም ፤ ማስቆጠር በምንፈልገው ልክ አላስቆጥርም። ያው ዋናው ነገር ዕድሎችን መፍጠሩ ስለሆነ ጥሩ ነው። ግቦቹን አስቆጥረን ነበር ግን የተሻሩበት መንገድ ለእኔ ግልፅ አይደለም። ግን ዋናው አለመሸነፍ ስለሆነ ጥሩ ነው።

ስለመስመር ተጫዋቾች አፈፃፀም

“አብዛኞቹ ተጫዋቾቼ አፈፃፀም ጥሩ ነበር። በምንፈልገው ደረጃ ውጤታማ መሆን አልቻልንም ውጤታማ መሆን የምንችለው የምናገኛቸውን ዕድሎች መጠቀም ስንችል ነው። ይህን ማድረግ አለመቻላችን ማሸነፍ በሚገባን ጨዋታ ነጥብ እንድንጋራ አድርጎናል።

ስለመጨረሻ ደቂቃዋ ቅጣት ምት

“ስሜታችን ጥሩ አይደለም ፤ የትኛውም ዓለም ላይ እንደምንመለከተው መሰል አጋጣሚዎችን አስመትተው ጨዋታ የተጠናቀቀም ከሆነ ሲያስቆሙ እንመለከት ነበር። በዚህ መልኩ መቆሙ ለእኔ አዲስ ነገር ነው ፤ ከእኛ በላይ ኃይለየሱስ ስለሚያቅ ለእሱ ብንተውለት የተሻለ ነው።”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

መሀል ሜዳ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ስለተወሰደባቸው ብልጫ

“በእኔ ዕይታ በመጀመሪያው አጋማሽ ያን ያህል ልዩነት አልነበረም። ሁለተኛው አጋማሽም ያንን ጠብቀን ለመሄድ ነበር የፈለግነው ኋላ ላይ ይሰሩ የነበሩ ስህተቶችን ለማረም ሞክረናል። የሚባክኑ ኳሶች በመቀነስ ረገድ ጨዋታ በማስቀጠል የተሻለ ነበር።”

የግብ ዕድሎችን ወደ ግብነት ስለመቀየር

“ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ የሚባለው በረኛውን ሲመልሰው ነው። ምናልባት ትርጉም የሌለው ኳስ መተህ በረኛው ቢይዘው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተብሎ ይመዘገባል ፤ ይሄ ለእኔ ትርጉም የለውም። ዒላማውን ጠብቆ ወደ ጎል መቀየር የሚችልም ኳስ መሆን አለበት። ምናልባት በረኛው የማይመልሳቸው ለጥቂት ወደ ውጪ የሚወጡ ኳሶችን በተወሰነ መልኩ ቢስተካከሉ ጎል የሚሆኑ ኳሶችም ከግምት ሊገቡ ይገባል። ከዚህም መነሻነት ይህኛው ስሌት ለእኔ ብዙም ስሜት አይሰጠኝም።”

“አጠቃላይ ብዙ የግብ ዕድሎችን አልፈጠርንም። ግን ይሄ ዒላማውን የጠበቀ ያልጠበቀ የሚለው ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ ጎል መሆን የማይችሉ ኳሶችን ወደ ጎል መተህ ዒላማውን የጠበቀ ተብሎ ይመዘገባል ይሄ ብዙ ትርጉም የለውም። እንደ አጠቃላይ ግን ዕይታው ሊቀየር ይገባል። ዒላማውን ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ጎል የሚቀየር ኳስ ነው ወይ በረኛው በቀላሉ የሚይዘው 50 ኳስ መምታት ይቻላል። ይሄ ዒላማውን የጠበቀ ተብሎ ቢቆጠር ብዙ ትርጉም የለውም።”