ሪፖርት | ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ በጠንካራ ፉክክር ታጅቦ በአቻ ውጤት ተገባዷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በሁለቱ የባህር ዳር ተከላካዮች ስም የተመዘገቡት ሁለቱ ጎሎች አዲስ አበባ እና ባህር ዳርን አቻ አለያይቷል።

በአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ አብዛኛውን ጨዋታ የሚቀርብበትን የ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ዛሬም ሲደግም ባህር ዳር ከተማ ደግሞ አዲሱ ተጫዋቹ ሔኖክ ኢሳይያስን በመጀመሪያ አሰላለፉ በማካተት በ4-2-3-1 ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ባህር ዳር ከተማ ኳሱን በተሻለ ለመቆጣጠር በመሞከር ሲንቀሳቀስ ስንመለከት ነበር። በተቃራኒው አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ የባህር ዳር የኳስ ቅብብል መሐል ሜዳ ሲደርስ እያጨናገፉ በአነስተኛ የኳስ ንክኪ ወደ ጎል ለመድረስ ሲጥሩ አስተውለናል። በዚህም በሩብ ሰዓት በሦስት አጋጣሚዎች የአቡበከር ኑሪን መረብ ለማግኘት ጥረት አድርገው ተመልሰዋል። ባህር ዳር ግን የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረገው በ20ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት ነበር።

አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስተናግድ የቀጠለወወ ጨዋታ በ29ኛው ደቂቃ የባህር ዳሩ የግብ ዘብ አቡበከር ኳስ በትክክል ለአጋሩ ማቀበል ባለመቻሉ የተሳሳተውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን ሳያስበው አግኝቶት ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ተቃርቦ ነበር። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተቃራኒ ሳጥን ሌላ አጋጣሚ ተፈጥሮ ጨዋታው ግብ ሊያገኝ ከጫፍ ደርሶ ነበር። በዚህም ፈቱዲን ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ፍፁም ዓለሙ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በአግባቡ ሳይቆጣጠር ቀርቶ ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭታ ወደ ውጪ ወጥታለች። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን አንድም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ53ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብ ተገናኝቶበታል። በዚህም ፍፁም ዓለሙ ያሻገረውን የመዓዘን ምት የመሐል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል በጥብቅ ምት በግንባሩ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ለጎሉ መቆጠር ምክንያት የሆነው ፍፁም ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ሞክሯል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ እጅግ ተነቃቅተው ምላሽ ለመስጠት መጣር የጀመሩት አዲስ አበባዎች በተደጋጋሚ የባህር ዳርን የግብ ክልል ለመጎብኘት ሲጥሩ ነበር። በተለይ ደግሞ በ63 እና 64ኛው ደቂቃ የሞከሩት ኳስ በአስቆጪ ሁኔታ ግብ ሳይሆን ቀርቷል። በቅድሚያ ሙሉቀን አዲሱ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፍፁም በግንባሩ ለማስቆጠር ሞክሮ አቡበከር እንደ ምንም አውጥቶበታል። ግብ ጠባቂው ያወጣውን ኳስ ከመዓዘን ምት ሲሻማ ደግሞ ሪችሞንድ አዶንጎ ከዛም እንዳለ ከበደ ወደ ግብ ቢመቱትም የባህር ዳሩ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከግቡ መስመር ኳሱን ከግብነት ታድጓታል። በ71ኛው ደቂቃም ፍፁም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ኳስ ልኮ መክኖበታል።

አዲስ አበባ ነቅሎ መውጣቱን ተከትሎ ባህር ዳር በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና ሽግግር ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን ለመግደል በማሰብ ሲጫወቱ አስተውለናል። በ75ኛው ደቂቃም ዓሊ ሱሌይማን ጥሩ ዕድል አግኝቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሳይጠበቅ ባህር ዳር ጎል አስተናግዷል። በዚህም ሰለሞን ወዴሳ ለግብ ጠባቂው አቡበከር ወደኋላ ያቀበለውን ኳስ የግብ ዘቡ ያለ ጫና የነበረ ቢሆንም ኳሱ በእግሮቹ መሐከል አምልጦት ግብ ተቆጥሯል። በጥሩ ሁኔታ የተነሳሱት የአሠልጣኝ ደምሰው ተጫዋቾች በ88ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ ከጫፍ ቢደርሱም ሪችሞንድ ኦዶንጎ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወደ ጨዋታው ሲገቡ የነበራቸውን አንድ ነጥብ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ይዘው የወጡት አዲስ አበባ እና ባህር ዳር ነጥባቸውን 15 እንዲሁም 21 በማድረስ 14ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።