የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-1 ባህር ዳር ከተማ


በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተነቃቃ ፉክክርን አስመልክቶን በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

በመጨረሻው ደቂቃ ስለተቆጠረችው ግብ እና ስለውጤቱ

“እውነት ነው የለፋንበት ቀርቶ ያለፋንበት ግብ ስለተቆጠረ ስሜቱ የተለየ ነበር። ከግቧ በኋላ ለውጦችን ካደረግን በኋላ ዕድሎችን መፍጠር ብንችልም መጠቀም ሳንችል ቀርተናል። ይህም ቢሆን መጥፎ የሚባል ውጤት አይደለም።

ስለ ሪችሞንድ አዶንጎ እንቅስቃሴ

“አዶንጎ ከዚህ በፊት የተረጋጋ ተጫዋች ነበር። ከሰሞኑ ግን እንድናሸንፍ ጉጉቶች አሉ። ከእሱም ብዙ እንደሚጠበቅ ያምናል ፤ እነዚህ ነገሮች እንዳይረጋጋ አድርገውታል።

ስለ ተከተላካይ መስመሩ

“አዎ በእርግጥ ተከላካዮቻችን ላይ እስካሁን ብዙ ጊዜ ክፍተቶች አሉ። ያንን ለመቅረፍ አዳዲስ ልጆች ወደ ቡድናችን እያመጣን ስለሆነ ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ።”


አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ግብ ስላስተናገዱበት መንገድ

“ኳሱን በመለሰው ተጫዋች እና በግብ ጠባቂው መካከል የነበረው የአዕምሮ ግንኙነት ጥሩ ነበር። መስተካከል የሚገባው ነገር ግን አቡበከር ኳሱን የተቀበለበት ቦታ ምናልባት ከግቡ አፋፍ ወጣ ያለ ቢሆን ኳሱ ቢያመልጠው እንኳን አደጋውን መቀነስ ይቻል ነበር ፤ ይህን ማስተካከል ይኖርብናል። ግብ ጠባቂዎች እዚህ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ትላልቅ ግብ ጠባቂዎች ሳይቀር መሰል ስህተቶችን ይሰራሉ። ዋናው ከዚህ ስህተት ተሞሮ የተሻለ ግብ ጠባቂ እንዲሆን መርዳት ነው። አቡበከር ጥሩ ወጣት ግብ ጠባቂ ነው ስለዚህ በቀጣይ ታርሞ የተሻለ ግብ ጠባቂ እንዲሆን እንሰራለን።

ሰለ አጥቂ መስመራቸው

“በመጀመሪያ አጋማሽ አልነበረም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከመሀል ሜዳው ስናልፍ ከመጀመሪያው በተሻለ በቁጥር በዝተን የማጥቃት ሚዛናችንን በማሻሻል ዕድሎችን መፍጠር ችለን ግብ አስቆጥረናል። የሚቀረን ነገር ያስቆጠርነውን ግብ ለማስጠበቅ የሄድንበትን መንገድ ማሻሻል ይገባናል።”