ጦሩ ጊኒያዊ አጥቂ አስፈርሟል

በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው መከላከያ አምስተኛ ተጫዋች የግሉ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከአብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ቀደም ብሎ ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ ጀምሮ ለሁለተኛው ዙር ውድድር ሲዘጋጅ የነበረው መከላከያ በዝውውር መስኮቱ እስራኤል እሸቱ፣ አሚኑ ነስሩ፣ ምንተስኖት አዳነ እና አሚን መሐመድን ማስፈረሙ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የ22 ዓመቱን የአጥቂ መስመር ተጫዋች ባዳራ ናቢ ሲላን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ታውቋል።

ከዋነኛ አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል ጋር በስምምነት ተለያይቶ የነበረው ክለቡ እንደጠቀስነው በቦታው እስራኤልን ቢያመጣም በአስተማማኝ ሁኔታ ቦታውን ለመሸፈን ጊኒያዊውን አጥቂ እንዳስፈረመ ይታሰባል። ለሀገሩ ክለብ ፌሎ ስታር ዴ ላቢ እና ለግብፁ አስዋን ተጫውቶ ያሳለፈው የመሐል አጥቂ ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ አበባ በመግባት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ ፊርማውን ለአንድ ዓመት ውል አኑሯል።