ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


በሦስተኛው የጨዋታ ቀን ምሽት ላይ የሚደረገውን ጨዋታ አስመልክተን ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በአንድ ነጥብ ልዩነት በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የተቀመጡት አዳማ እና ወልቂጤ በእንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቅ ጨዋታ ያከናውናሉ። የመጀመሪያውን ዙር በሽንፈት የጨረሰው ወልቂጤ ከተማ ከሰንጠረዡ ወገብ ከፍ እንዲል የሚያስችሉትን ነጥቦች ከነገው ጨዋታ ይጠብቃል። ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው የመጣላቸው አዳማዎች በበኩላቸው ዛሬ ነጥብ የጣለው የባህር ዳርን 6ኛ ደረጃ ለመያዝ የሚረዳቸውን ጨዋታ ያደርጋሉ።

የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገው ዙሩን የጨረሱት ወልቂጤዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ድል አይቅናቸው እንጂ ጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኙ ነበር። ሊጉ በረጅም ዕረፍት ከተቋረጠ በኋላ ከመጋቢት 04 ጀምሮ ዝግጅታቸውን ያከናወኑ ሲሆን ሮበርት ኦዶንካራ እና ቤዛ መድኅንን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለው ወደ ውድድሩ ተመልሰዋል። ከነገ ተጋጣሚው በሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ዝግጅቱን የጀመረው አዳማ ከተማ በቀጣዮቹ ቀናት አዳዲስ ዝውውሮችን እንደሚፈፅም ሲጠበቅ ለጊዜው አዲስ የሚሆነው እንደ ክለብ ከዩናይትድ ቤቨሬጅ ጋር የፈፀመው የስፔንሰር ሺፕ ስምምነት ይሆናል።

ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን የመጀመሪያው ዙር ሊያልቅ ሦስት ጨዋታዎች ሲቀር የቀጠረ ሲሆን አራት ነጥቦችንም አሳክቷል። በሊጉ በርካታ ግቦችን በማስተናገድ ከሀዲያ ጋር አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ መጠነኛ መሻሻልን አሳይቷል። ግቦችን ከመቀነስ ባለፈም በአጨዋወት ደረጃ ቡድኑ በተለይም ከኳስ ውጪ ጉልበት ጨምሮ መታየቱ ለሁለተኛው ዙር ተስፋ የሚሰጠው ነው። ከዚህ በተለየ የሊጉ ሁለተኛ ጠንካራ የመከላከል አቅም ባለቤት የሆነው አዳማ ከተማ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የመርጋቱ ሚስጥርም የኸው ጠንካራ ጎኑ ይመስላል። ግብ በማስቆጠሩ ደከም ያለ ቁጥር ያለው አዳማ እንደ ኋላ መስመሩ ብርታት ባይሆን በአቻ ውጤት ከጨረሳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች በተወሰኑት ያለነጥብ የመውጣት ዕድል ሊገጥመው በቻለ ነበር።

ከቡድኖቹ የጨዋታ ባህሪ እና ሌሎች ጉዳዮች አንፃር ስንመለከተው የነገው ጨዋታ መልካም ፉክክር እንደሚታይበት ይገመታል። ለቅድመ ውድድር ዘመን የቀረበ ርዝመት የነበረው የዕረፍት ጊዜ የተሻሻለ ወልቂጤን እንድንጠብቅ ያደርገናል። አሰልጣኝ ተመስገን እንደ አዲስ አሰልጣኝ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተደራራቢ ጨዋታ ርቀው ቡድናቸውን በራሳቸው መልክ የማዘጋጀት ዕድል በማግኘታቸው ወልቂጤ በጥሩ ጎኑ ፍንጭ የሰጠባቸው ባህሪዎቹ ይበልጥ ተሻሽለው እንዲመጡ በር ይከፍታል። በዚህም መሀል ላይ በቶሎ ኳስ ለማስጣል የሚለፉ አማካዮች እና ከኳስ ጋር በፈጣን ቅብብል ወደ አዳማ ሳጥን ለመድረስ የሚጥር አጠቃላይ የቡድን መዋቅር ከወልቂጤ ይጠበቃል።

ወልቂጤዎች በዚህ አኳኋን ከባድኑን የአዳማ የኋላ ክፍል መግጠማቸው ብቻ ሳይሆን የአዳማዎችም ምላሽ ለጨዋታው ድምቀት መነሻ ሊሆን ይችላል። ቡድኑ ውድድሩን ሜዳው ላይ እንደማድረጉ ይበልጥ በማጥቃት እሳቤ ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ሲጠበቅ መሀል ላይ የወልቂጤን የኳስ ውጪ ጫና የሚመጥን ታታሪ የአማካይ ክፍል መያዛቸው የመሀል ሜዳውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። በተናጠል ጥሩ የግል ብቃት ያላቸው የአዳማ አጥቂዎችም እንደ ቡድን የሚኖራቸው አቋም የወልቂጤን የተሻሻለ የኋላ ክፍል የመፈተን አቅሙ ምን ያህል እንደሚሆን ለመመልከት በሰራተኞቹ ሳጥን ዙሪያ የሚፈጠሩ የአንድ ለአንድ ቅፅበቶች ትኩረት ሳቢ መሆናቸው አይቀርም።

ወልቂጤ ከተማ አዲስ ያስፈረማቸው ሮበርት ኦዶንካራ እና ቤዛ መድኅን የወረቀት ጉዳያቸው አልቆ ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ እርግጥ አልሆነም። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ረመዳን የሱፍ እና ቅጣቱን የጨረሰው ዮናስ በርታን በመጠነኛ ጉዳት ሳቢያ በነገው ጨዋታ አያሰልፍም። በአዳማ ከተማ በኩል ግን የተመዘገበ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለም።

ጨዋታውን ሚካኤል ጣዕመ በመሀል ዳኝነት ፣ ሻረው ጌታቸው እና እያሱ ካሳሁን በረዳትነት እንዲሁም ኃይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ እስካሁን በተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ነጥብ ሲጋሩ ወልቂጤ ከተማ አንድ ግዜ አሸንፏል። በሦስቱ ጨዋታዎች ወልቂጤ ሁለት አዳማ ደግሞ አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

– ሊጉ ከረጅም ከዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።