አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዘንድሮው የውድድር አመት በመጀመሪያው ዙር ደካማ ጉዞን በማድረግ በሰንጠረዡ ወራጅ ቀጠና ላይ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ዙሩን የፈፀመውን ጅማ አባጅፋር የሁለተኛውን ዙር ውድድርን የፊታችን ቅዳሜ ሀዋሳ ከተማን በመግጠም ይጀምራል፡፡ ካለበት ደረጃ ፈቀቅ ብሎ ለማጠናቀቅ ይረዳው ዘንድ ሦስት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ በውሰት ውል እስከ አመቱ መጨረሻ በዛሬው ዕለት በፌድሬሽን ፅህፈት ቤት በማስፈረም የግሉ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
አጥቂው ጫላ በንቲ ወደ አባጅፋር አምርቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ 2005 ላይ ከተገኘ በኋላ በመከላከያ ተስፋ ቡድን ፣ በነቀምት ከተማ እና በሀምበሪቾ ዱራሜ በመጫወት ቆይታ የነበረው ሲሆን ከ2011 ጀምሮ ያለፉትን አራት አመታት ለቡራዩ ከተማ በመጫወት አሳልፏል፡፡በዘንድሮ የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ላይ ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው ይህ ተጫዋች ኢትዮጵያ ቡናን ለመቀላቀል ጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ማረፊያው አባጅፋር ሆኗል፡፡
አስጨናቂ ፀጋዬ ሁለተኛው በውሰት ውል ወደ ጅማ አምርቷል፡፡ ከአርባምንጭ ከተማ ከተገኘ በኋላ ለዋናው ቡድን ግልጋሎት መስጠት የቻለ ሲሆን በሀምበሪቾ ዱራሜ እና ዘንድሮ ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ጋሞ ጨንቻ ሲጫወት የነበረው የተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለውን ክለብ በውሰት ውል ተቀላቅሏል፡፡
ሦስተኛው ተጫዋች ቦና አሊ ነው፡፡ ከአምቦ ጎል ፕሮጀክት የተገኘው እና በሻሸመኔ ከተማ ያለፉትን ዓመታት ማሳለፍ የቻለው አጥቂው ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ልዩነት በመፍጠር የተለያዩ ክለቦችን ቀልብ መሳብ ቢችልም ማረፊያው አባጅፋር ሆኗል፡፡