ሪፖርት | ወልቂጤ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


አዝናኝ ፉክክር ያስመለከተን የወልቂጤ ከተማ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ሁለቱም ተጋጣሚዎች በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

ከጅምሩ ጥሩ ፉክክርን ማሳየት በጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ኳስ መስርተው በመውጣት በማጥቃት እሳቤ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። አንዳቸው የሌላኛቸውን የኳስ ፍሰጥ ለማቋረጥ በትጋት የተንቀስልቀሱ ሲሆን ወደ ሁለቱ ሳጥኖች የሚላኩ ረዘም ያሉ አደገኛ ኳሶችም በርከት ብለው ይታዩ ነበር።

በወልቂጤ በኩል ከአብዱልከሪም ወርቁ የሚነሱ ኳሶች ወደ ፊት ሲላኩ የአዳማ ተከላካዮች በንቃት ሲያወጡ ታይቷል። አዳማዎች በበኩላቸው በተለይ ከቀኝ መስመራቸው ከጀሚል ያዕቆብ እና አቡበከር ወንድሙ በሚነሱ ኳሶች ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ጫናዎችን ፈጥረዋል።

ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ያሳይ እንጂ ከባድ የሚባል ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳይፈጠርበት ቆይቶ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ተከታታይ ግቦች ተቆጥሮበታል። 26ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ተሻገር አዳማዎች የኳስ ምስረታ ላይ ሳሉ ከደስታ ዮሐንስ ያስጣለውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ቀዳሚዋን ግብ አስቆጥሯል። ሆኖም 31ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮች ሲያወጡት በቀኝ መስመር ሆኖ የደረሰው አቡበከር ወንድሙ በጥሩ ሁኔታ ዳግም ወደ ሳጥን ሲልከው ራሱን ነፃ አድርጎ የቆመው አዲስ ተስፋዬ በግንባሩ ግብ አድርጎት አዳማን አቻ አድርጓል።

ከግቦቹ በኋላ የጨዋታ ግለት ይበልጥ ከፍ ብሎ የቡድኖቹ ፍልሚያ ለዐይን ማራኪ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይም ወልቂጤዎች ይበልጥ ለግብ ሲቀርቡ 37ኛው ደቂቃ ላይ ጀማል ጣሰው ከግብ አስቆጣሪው አዲስ ተስፋዬ ወደ ኋላ የደረሰውን ኳስ መቆጣጠር ተስኖት ግብ ሊቆጠር ቢቃረብም ቶማስ ስምረቱ ደርሶ አድኖታል። አዳማዎችም እንዲሁ በፈጣን ጥቃቶች የወልቂጤ ሳጥን መግቢያ ላይ የደረሱባቸው አደገኛ ቅፅበቶች ቢታዩም አጋማሹ ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በ 1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ የቀደመ ግለቱን ይዞ ባይቀጥልም የአዳማዎች ብልጫ ተንፀባርቆታል። ተጋጣሚያቸውን ወደራሱ ሜዳ መግፋት የቻሉት አዳማዎች የመሀል ሜዳውን የበላይነት በመውሰድ ጨዋታውን ከመቆጣጠር ባለፈ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ቀርበው ነበር። 51ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ጎበና ከቅጣት ምት ያሻገረውን ዮናስ ገረመው በግንባሩ ሞክሮ ሰዒድ ሀብታሙ ለጥቂት አውጥቶበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የዮናስ ገረመው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በአሜ መሀመድ ተሞክሮ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ጋር ወጥቷል።

ወልቂጤ ከተማዎች ቀስ በቀስ ለመልሶ ማጥቃት በቀረቡ ኳሶች ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው እንዳሰቡት እንዲያደርጉ አልፈቀዱላቸውም። ይልቁኑም በአዳማዎች በኩል 69ኛው ደቂቃ ላይ የዳዋ የቀኝ መስመር ቅጣት ምት ዳግም ንጉሴ ሲያርቀው አሜ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ወደ ግብ የላከውን ሰዒድ ሀብታሙ በአስገራሚ ሁኔታ አድኖታል።
ወልቂጤዎች የቀደመ የጨዋታ ምታቸውን ወደ መጨረሻው ላይ ማግኘት ችለዋል። ቡድኑ ከተጨዋቾች ለውጥ በኋላ አማካይ ክፍል ላይ አዳማዎችን መቆጣጠር ሲችል ተቀይሮ በገባው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ንክኪ እንዲሁም በአብዱልከሪም ወርቁ እና ጌታነህ ከበደ የርቀት ሙከራዎች አሸናፊዋን ግብ ለማግኘት ጥሯል።

በጭማሪ ደቂቃዎችም የምሽቱ ጨዋታ አስደንጋጭ ሙከራዎችን አስመልክቶናል። የአዳማ ከተማው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የላከው እና አቡበከር ሳኒ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚዎች የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ዕድል ሆነው አዝናኙ ፍልሚያ 1-1 ተጠናቋል።

በውጤቱ አዳማ ከተማ በ22 ነጥቦች 6ኛ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ21 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።