ለገጣፎ ለገዳዲ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጓል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ለገጣፎ ለገዳዲ ሰንዳፋ በኬን መርታቱን ተከትሎ በ2015 የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።

ዘንድሮ በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እየተካሄደ በቆየው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ውስጥ ተደልድሎ ውድድሩን ሲያደርግ የነበረው እና ከዚህ ቀደም ከ2010 አንስቶ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ እና ዳዊት ሀብታሙ መሪነት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት ተቃርቦ ሲመለስ የነበረው ለገጣፎ ለገዳዲ ዘንድሮ ግን ውጥኑ በወጣቱ አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ አማካኝነት ሰምሯል።

ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን ምድቡ እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ አዳጊው ቡድን ተለይቶ ያልታወቀ ሲሆን በመጨረሻው የጨዋታ ዕለት ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከኮልፊ ቀራንዮ በሼር ሜዳ እንዲሁም ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ሰንዳፋ በኬ በባቱ ስታደዮም በአንደኝነት ለመጨረስ የተደረገው ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ ያስገደደ ነበር።

በባቱ ስታዲየም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሪሽን ምክትል ፀሀፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴን ጨምሮ የኦሮሚያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሀላፊ አቶ ፊሮምሳ ለገሰ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች በክብር እንግድነት በታደሙበት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክርን ሳያስመለክት ቢዘልቅም በአጋማሹ ለገጣፎች ፍፁም የበላይ ነበሩ።

ገና በጊዜ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ለገጣፎዎች በ4ኛው ደቂቃ በልደቱ ለማ አማካኝነት ግብ ቢስቆጥሩም ከጨዋታ ውጭ በሚል ተሽሮባቸዋል ፤ የተወሰደባቸውን ጫና ለመቋቋም ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ሰንዳፋዎች በ8ኛው ደቂቃ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። አጥቂው ልደቱ ለማ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኪሩቤል ወንድሙ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ አሳርፏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የፊት መስመር አጥቂው ልደቱ ለማ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የቡድኑን ሁለተኛ ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷ ግን የግቡን የላይኛው አግዳሚ ለትማ ወጥታለች። በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ የተሻሉት የነበሩት ለገጣፎዎች የሚደርጉትን የግብ ሙከራዎች በማዳን የሰንዳፋ በኪው ግብ ጠባቂ እያሱ ተካ ስራ በዝቶበት ውሏል። በ38ኛው ደቂቃ በድጋሚ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ የተከላካዮች ስህተት ታክሎበት የደረሰው ታታሪው አጥቂ ፋሲል አስማማው የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ እምብዛም የአጨዋወት እንቅስቃሴ ለውጥ ያላስመለከተን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነበር። በተለይም ለገጣፎዎች አማካይ ተጫዋቾችን በማብዛት ከርቀት በሚልኳቸው ኳሶች የሰንዳፋን በኬን ግብ ለመፈተሽ ጥረት ሲደርጉ ቆይተዋል። ይህም ትጋታቸው በ56ኛው ደቂቃ ዳዊት ቀለመወርቅ አክርሮ በመምታት የቡድኑን ሦስተኛ ጎል እንዲያስቆጥር ምክንያት ሆኗል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ልዩነቱን ለማጥበብ ሰንዳፋዎች ወደ ለገጣፎ የግብ ክልል እየደረሱ ጥረት ቢደርጉም ሳይቀናቸው ቀርቷል። ይባስ ብሎ በ75ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን የግብ እድል ልደቱ ለማ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ወደ አራት ከፍ አድርጉታል።

ጨዋታው በለገጣፎ ለገዳዲ የ4-0 የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሽልማት መርሐ-ግብር ተከናውኗል። በሼር ሜዳ የተከናወነው የሽልማት መርሐ-ግብር በከተማው ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ትብብር ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት በማበርከት ጅማሮውን አድርጓል።

በመቀጠል በልዮ ተሸላሚነት የቤንጂ ማጂ ቡና የህክምና ባለሙያ ኤርምያስ እና የቡራዩ ከተማው የሙያ አጋሩ ጀርመን ኤሪኳ ወጌሻ ላጡ ተጫዋቾች በቅንነት በማገልገል ላሳዩት ቀና ተግባር የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል ፤ በውድድሩ ኮከብ ተጨዋች እና አሰልጣኝ ሌላው ምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው አካላት ነበሩ።

ከምስክር ወረቅት ስነ ስርአት በኋላ ወደ ሜዳሊያ ሽልማት ያመራው መርሐ-ግብሩ በእለቱ ሁለቱን ጨዋታዎችን ለመሩት ዳኞች ሜዳሊያ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይነትም ውድድሩን በሦስተኝነት ያጠናቀቁት ቡራዩ ከተማዎች የነሀስ ሜዳሊያ ሁለተኛ ሆነው የጨረሱት ቤንች ማጂዎች የብር ሜዳሊያ ሲወስዱ የውድድሩ ሻምፒዮና የሆኑት ለገጣፎ ለገዳዲዎች የወርቅ ሜዳሊያ እና የምድብ ሀ አሸናፊነታቸውን የሚያረጋግጥ የዋንጫ ሽልማት ተረክበዋል።